ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባርና ንቅናቄ ይፋ አደረጉ

ሚያዝያ 18/2016 (አዲስ ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር አዲስ ተግባርና ንቅናቄ ይፋ አድርገዋል።

የማኅበረሰቡን የጽዳት ባህል ክብርን የጠበቀ ለማድረግ የተወጠነው ይህ ተነሣሽነት፣ መጸዳጃ ቤቶችን ዘመናዊ በሆነ መልኩ መገንባት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።

“ጽዱ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተነሣሽነት “ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” በሚል መሪ ሀሳብ በገንዘብ ወይም በዓይነት የኅብረተሰብ ደጋፍ እንደሚሻ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረት ከተሰጠባቸው ነገሮች አንዱ ጽዱ እና አረንጓዴ ከባቢ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

 

“ክብር ያለው የንጽህና ባህል መፍጠር ይኖርብናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተገቢው ቦታ ክብርን ጠብቆ መጸዳዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ለዚህ ደግሞ ሥርዓት ማበጀት እና የመጸዳጃ ቦታ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በማስተማር እና ሕግ በማስከበር ሥርዓቱን ማሳደግ እንዲሁም የመጸዳጃ ቦታን መገንባት ይጠበቅብናልም ብለዋል።

“በዚህ መልካም ተግባር ላይ ኢትዮጵያውያን ከተማችንን ጽዱ፤ አረንጓዴ እና ውብ ለማድረግ ከጎናችን እንደምትቆሙ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል።

 

ይህንንም ለማሳየት አንድ ናሙና ተገንብቶ እንደ ማሳያ በመዲናዋ መቀመጡንም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በከተማዋ በርከት ያሉ የመጸዳጃ ቤቶች ለመገንባት ኢትዮጵያውያን በገንዘብ አልያም በመገንባት እንዲተባበሩም ጥሪ አቅርበዋል።