በደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ1 ሚሊየን አለፈ

ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ አገራት መካከል ከአንድ ሚሊየን በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎችን በመመዝገብ ቀዳሚዋ ሆነች።

ይህ የሆነው የአገሪቱ ባለሥልጣናት በፍጥነት የሚስፋፋው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በአገሪቱ ውስጥ መገኘቱን ይፋ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ነው።

የተወሰኑ የደቡብ አፍሪካ ሆስፒታሎች እንዲሁም የሕክምና ማዕከላት በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሕሙማንን እየተቀበሉ መሆኑን ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም ለኮሮናቫይረስ መከላከል የተመደበው ሀብት ላይ አደጋን ደቅኗል ነው የተባለው።

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቫይረሱ ይበልጥ እንዳይሰራጭ ለማድረግ ጠበቅ ያለ የእቅንቅስቀሴ ገደብ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እሁድ ዕለት የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር ዝዌሊ ምክሂዜ ይህንን አሳዛኝ ዜና ለአገራቸው ሕዝብ ይፋ አድርገዋል።

አሁን ደቡብ አፍሪካ 1,004,413 በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መኖራቸው በምርመራ ያረጋገጠች ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ 26,735 ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ባለፈው ሳምንት ብቻ 11,700 ደቡብ አፍሪካውያን በአንድ ቀን በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀ ሲሆን፣ በዚህ የተነሳም ከቀደመው ሳምንት ጋር ሲነጻጸር በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ39 በመቶ እንዲጨምር አድርጎታል።

ከረቡዕ እስከ አርብ ድረስ ባሉት ቀናትም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በ14,000 መጨመሩ ተገልጿል።

በደቡብ አፍሪካ አዲሱ 501.ቪ2 በመባል የሚታወቀው የኮሮናቫይረስ ዝርያ ስርጭቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨመር እንዳደረገው ይታመናል።

ይህ ዝርያ በደቡብ አፍሪካውያን ተመራማሪዎች በምሥራቃዊ ኬፕ አውራጃ እና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑ ተደርሶበታል።

ከዚህ ሳምንት ቀደም ብሎ በዚሁ አዲስ የቫይረስ ዝርያ ምክንያት ዩናይትድ ኪንግደም ከደቡብ አፍሪካ የሚመጡ መንገደኞች ላይ እገዳ ጥላለች።

በዩናይትድ ኪንግደም አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መገኘቱ ይታወሳል።

ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳችው አፍሪካዊት አገር ሞሮኮ ስትሆን 432,079 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከእነዚህም መካከል 7,240 ያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

በመቀጠል ግብጽ 131,315 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲረጋገጥ 7,352 ሞተዋል፤ በተመሳሳይ በቱኒዚያም 130,230 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ሲረጋገጥ 4,426 ሕይወታቸውን አጥተዋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡