ፌዴራል ፖሊስ ለዒድ አል አድሃ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

ፌዴራል ፖሊስ

ሐምሌ 12/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ለመላው ሕዝበ ሙስሊም እንኳን ለ1 ሺህ 442ኛው ዒድ አል አድሃ /አረፋ/ በዓል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ ታላቅ ክብረ በዓል በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ሕዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የፀጥታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።

በዓሉ ሁለተኛ ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት በስኬት እና በሰላም በተጠናቀቀበት ማግስት የሚከበር በዓል በመሆኑ ደስታውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ብሏል ኮሚሽኑ።

መላው የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኃይል ከሌሎች ፀጥታ እና ደህንነት አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ በሰላም እና በድምቀት እንዲከበር በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ገልጿል።

መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓሉ ያለምንም ፀጥታ ችግር በደስታ እና በፍቅር እንዲከበር ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የበኩላችሁን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።