ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከክልሉ ፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በመተከል ዞን ግልገል በለስና ማንዱራ አካባቢ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ እና ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የፈጥኖ ደራሽ ም/ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ይስሃቅ ኣሎ በመተከል ዞን ግልገል በለስና ማንዱራ አካባቢ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልሉን የፀጥታ ኃይሎችን በስፍራው በመገኘት እየተሰራ ያለውን የፀጥታ ሥራ ገምግመዋል፡፡ እንዲሁም ሰራዊቱ ያለበትን ቁመናና ሁኔታ በመዘዋወር ተመልክተዋል፡፡
ኃላፊዎቹ ከጉምዝ ታጣቂዎች እና ከሕወሓት ተላላኪ ቡድኖች ጋር በስምሪት እየተፋለሙ ካሉ ጀግና የሰራዊት አባላት ጋር ሰፊ ውይይትም ማድረጋቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ም/ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በቦታው ለተሰማሩት የሰራዊት አባላት የሚሆን 20 ሰንጋዎችንና የተለያዩ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ማኔጅመንትን በመወከል አስረክበዋል፡፡