ቻይና የቡድን ሰባት ሀገራት ዲሞክራሲን ለማስተማር ብቁ አይደሉም አለች

ታኅሣሥ 13/2014 (ዋልታ) በሆንግ ኮንግ በተደረገ የሕግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ማዕከላዊ መንግስትን የሚደግፉ ዕጩዎች አሸንፈዋል፡፡

በምርጫው የማዕከላዊ ቻይና መንግሥት ደጋፊ የሆኑ ዕጩዎች ያሸነፉ ሲሆን ይሄንንም ተከትሎ ምዕራባዊያን አገራት የሆንግ ኮንግ ምርጫን ዴሞክራሲያዊ አይደለም በሚል ትችቶችን በመሰንዘር ላይ ሲሆኑ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዛኦ ሊጂያን እንዳሉት አውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ የቡድን ሰባት አባል አገራት ዴሞክራሲን ለማስተማር ብቁ አይደሉም፡፡

ዴሞክራሲ ለምዕራባዊያን ሀገራት የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በሌላ ሉዓላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት መንገዳቸው መሆኑንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

ባሳለፍነው እሁድ በቻይና አንድ አካል በሆነችው ሆንግ ኮንግ ግዛት የተካሄደውን የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ በማጣጣል ላይ ናቸው የሚሉት ቃል አቀባዩ ምዕራባዊያን ይሄንን የሚያደርጉት ምርጫው እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ባለመሄዱ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የቡድን ሰባት አባል አገራት ስለ ዴሞክራሲ ከማውራታቸው በፊት በመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን እና በአገራቸው ያሉተን የፖለቲካ ውጥረቶችን ጨምሮ በዜጎቻቸው መካከል ያለውን መድሎ ለማስቆም ይስሩ ሲሉም ወርፈዋል፡፡

በሆንግ ኮንግ በተካሄደው የታችኛው የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ የቻይና ማዕከላዊ መንግስትን አቋም የሚደግፉ እጩዎች 90 በመቶውን መቀመጫ ያሸነፉ ሲሆን የምርጫው ውጤት ምዕራባዊያንን አላስደሰተም፡፡

የምዕራባዊያን አገራት ባሳለፍነው እሁድ በተካሄደው ምርጫ ላይ የቻይና ማዕከላዊ መንግስት ተጽዕኖ አድርጓል፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ ነው እና ሌሎች ትችቶችን በቤጂንግ ላይ ሰንዝረዋል፡፡

ሆንግ ኮንግ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረች ሲሆን ከፈረንጆቹ 1997 ዓመት ጀምሮ ቻይና ተረክባ በማስተዳደር ላይ ስትሆን አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን አገራት ሆንግ ኮንግ የቻይና አካል አይደለችም በሚል ቀጥታ ግንኙነት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ይህ ድርጊት ቻይናን ያስቆጣ ሲሆን በየጊዜው አሜሪካ እና ምዕራባዊያን አገራት ከቻይና የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን እንዲሰበስቡ በማጠንቀቅ ላይ እንደምትገኝ የአልዐይን ዘገባ ያመለክታል፡፡