የካቲት 28/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ አህጉራዊ ውድድር ማስተናገድ የሚችል የዋና ገንዳ ሊገነባ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በኮምቦልቻ ከተማ የውሃ ዋና ማዘውተሪያ ስፍራ ለመገንባት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የቦታ ርክክብ አድርጓል፡፡
የ2013 የኢትዮጵያ ክልሎችና ክለቦች ውሃ ዋና ሻምፒዮና በአማራ ክልል አስተናጋጅነት በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በስፍራው የሚገኙት የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚዎች ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመወያየት ደረጃውን የጠበቀ የውሃ ዋና ማዘውተሪያ ስፍራ ለመገንባት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡
የውሃ ዋና ማዘውተሪያው የሚገነባበትን ቦታ መርጠው ከከተማ አስተዳደሩ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ተረክበዋል፡፡ በአገር አቀፍ ውድድሮች ሁሌም ውጤት የሚያስመዘግቡና በኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን ወክለው የታዩ ዋናተኞችን ላፈራችው ኮምቦልቻ ከተማ ተጨማሪ የውሃ ዋና ማዘውተሪያዎችን መገንባት ለነገ የሚባል ስራ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመሆን በፍጥነት ወደስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውንም ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ሶርሳ በመግለጫው ላይ እንዳሉት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ በቀናነት ላስተናገዳቸው የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምስጋናቸውን በማቅረብ የውሃ ዋና ማዘውተሪያው መገንባት በአለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉና ውጤት የሚያስመዘግቡ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ አቃቤ ነዋይ አቶ ዳግም ዝናቡ በበኩላቸው አህጉራዊ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚችል ደረጃውን የጠበቀ የውሃ ዋና ማዘውተሪያ እንዲሆን ለማድረግ ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡
(በፍስሀ ጌትነት)