ሚኒስቴሩ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከዘርፉ ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ማቀዱን አስታወቀ

የማዕድን ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ

የካቲት 29/2013 (ዋልታ) – የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከዘርፉ ከ17 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው ከተቋሙ፣ ከተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ጋር የዘርፉን የሰባት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ከባለፈው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም በተሻለ ሁኔታ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉንም ገልጿል፡፡

በተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ተግባራት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የማዕድን ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ገልጸዋል።

መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት የሠጠው በመሆኑ አመራሩና ሠራተኛው በጋራ ተናቦ በመስራት የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ መወጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በመድረኩ የቀጣይ 5 ወራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የሲቪል ሠርቪስ ፍኖተ ካርታም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ውስጥ በህዝብ በሚመረጥ መንግሥት የሚነድፋቸውን የልማት ዕቅዶች ማሳካት የሚችል፣ የህዝብ አገልጋይነትን መንፈስ የተላበሰና ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያለው የመንግስት አገልግሎት ስርዓት መገንባት የፍኖተ ካርታው ዋናው ዓላማ መሆኑንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡