ሰኔ 30/2013 (ዋልታ) – በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን በመወከል የምትወዳደሩ አትሌቶች የአበበ ቢቂላን አኩሪ ታሪክ ለመድገም መዘጋጀት አለባችሁ ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ጋር በመሆን በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ዝግጅት በኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ ተገኝተው ተመልክተዋል።
የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሁሉም ተወዳዳሪ በቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊ በመሆን ሀገሩን ዳግም በከፍታ ላይ ማስቀመጥ እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ብዙ ተዓምር የሰራች ሀገራ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቷ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች ይህንኑ ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል።
አትሌቶች የአገራቸው አምባሳደር በመሆናቸው በሄዱበት ሁሉ በማሸነፍ ኢትዮጵያን ከፍ እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አደራ ብለዋል።
ተወዳዳሪዎቹ የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
የኦሎምፒክ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሼቦ እና አትሌት ሰለሞን ባረጋ በበኩላቸው፣ ላለፉት 8 ወራት በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
እ.ኤ.አ በ1964 አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበውን ታሪክ ለመድገም ጠንካራ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሻምበል አበበ በቂላ በ1964 በቶክዮ ጃፓን በተካሄደው ውድድር የራሱን ክብረወሰን በማሻሻል ነበር አሸናፊ የሆነው።
የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 23 ቀን 2021 በጃፓኗ ቶኪዮ ይጀመራል።