ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰንደቅ አላማ የሀገርን ታሪክ በደማቅ ማህተብ ያኖረ የሉአላዊነት መገለጫ ነው አሉ

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጥቅምት 7/2015 (ዋልታ) ሰንደቅ አላማ የሀገርን ታሪክ በደማቅ ማህተብ ያኖረ የክብር እና የማንነት እንዲሁም የሉአላዊነት መገለጫ መሆኑን የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

የሰንደቅ አላማ ቀን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እና ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል::

ፕሬዝዳንቷ በአያት ቅድመ አያቶቻችን ተጋድሎ ለተረከብነው ሰንደቅ አላማችን ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የአንድነት፣ የህብረት እና የህብረ ብሄራዊነት የመተጋገዝ እና የመተሳሰብ እሳቤ በሰንደቅ አላማ ምልክት ውስጥ የታተመ በመሆኑ በተግዳሮቶችም ይሁን በድሎች አንድነትን መታወቂያችን እና መድመቂያችን ልናደርግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ሰንደቅ አላማችን የደም እና የአጥንት ዋጋ በመሆኗ ከነሙሉ ክብሯ ለመጠበቅ አሁን በውስጥም በውጭም ኢትዮጵያ ላይ የተቃጡብንን ተግዳሮቶች መመከት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሄብሮን ዋልታው