ፕሬዝዳንት ባይደንና ፑቲን በሳይበር ደህንነት ላይ ሊወያዩ ተስማሙ

ሰኔ 10/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በጦር መሳሪያ ቁጥጥር እና በሳይበር ደህንነት ዙሪያ ውይይት ለመጀመር መስማማታቸው ተገለጸ፡፡

መሪዎቹ በትናንትናው ዕለት በጄኔቫ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን በሳይበር ደህንነት፣ በጦር መሳሪያ ቁጥጥር፣ በሩሲያው ተቃዋሚ  አሌክሲ ናቫልኒ ዕጣ ፈንታ እና በቀጣይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ዙሪያ ተወያይዋል፡፡

በተጨማሪም መሪዎቹ እስር ላይ በሚገኘው የሩሲያ ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ ጉዳይ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላቸው ተጠቁሟል፡፡

ፕሬዝዳንት ባይደን ተቃዋሚው አሌክሲ ናቫልኒ በእስር ቆይታው ላይ ህይወቱን የሚያሳጣ አንዳች ነገር ቢከሰት ውጤቱ ጥሩ እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ከ2020 በተካሄደው የአሜሪካ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ከሁለቱም ሀገራት ወጥተው የነበሩት አምባሳደሮች እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡