ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – ከ500 ሺህ በላይ የስፖርት ቤተሰቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃግብር ተጀመረ።
“የስፖርት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ ያበበች ፣ በሰብአዊነት ላይ የተገነባች አዲስ አበባን እንፈጥራለን” በሚል በመስቀል አደባባይ በይፋ ተጀምሯል።
ለቀጣይ 3 ወራት የሚቆየው መርሃ ግብሩ ከ500 ሺህ በላይ የስፖርት ቤተሰቦች በችግኝ ተከላ፣ በሰብዓዊ ተግባራት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት እና ልዩ ልዩ ተግባራት እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን ገልፀዋል ።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ2 ሺህ 200 በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች ማዕድ ማጋራት ፣ ለ50 የተመረጡ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ፣ ስፖርታዊ ስልጠና ፣ስፖርታዊ ውድድሮች ፣እና ማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ሌሎችም ተግባራቶች ይከናወናሉ ተብሏል።
መርሃ ግብሩ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ፣ ጉልበት፣ እውቀትና በቁሳቁስ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትና 30 ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎች በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ መገለፁን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።