አሁን ለመጣው ለውጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ሊተጉና ሊተባበሩ ይገባል- ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – አሁን ለመጣው ለውጥ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው ሊተጉ እና ሊተባበሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለሰ አለሙ በተገኙበት ከከተማዋ ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች እና ለመከላከያ ሠራዊት በሚደረገው ድጋፍ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይት መድረኩ ኢትዮጵያውያን ደስታችን ሙሉ የሚሆነው ሁሉም እጅ ለእጅ መያያዝ ሲኖረን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ እኛ ስንተባበር እና ስንተጋገዝ የማናሳካው ጉዳይ እንደሌለ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ተግባራት ጉልህ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ወጣቶች በጁንታው ርዥራዦች የሚነዛውን የውሸት የማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ  ወደ ጎን በመተው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚችሉት አቅም ማገዝና ደጀንነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ለማሳየት በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ በማጠናከር ረገድ እያደረገ ያለው ተግባር ለሠራዊቱ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ያለ አንዳች ሁከት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ  ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ወጣቶች የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስጠበቅ ሌት ተቀን በመጠበቅ  መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።