11ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከነገ ጀምሮ ይከበራል

ሚያዚያ 05/2013 (ዋልታ) – 11ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በጃን ሜዳ እንደሚከበር ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተክሉ ሹክሪ እንደገለፁት 11ኛው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት “ሙያ ሃብት ነው” በሚል መሪ ቃል ነው የሚከበረው።

የሰው ሃይል ማብቃት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዋና ተልዕኮዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ መደበኛ ተማሪዎች ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ጥራትን ለማምጣት በተደረገው ጥረት በ18 ሙያዎች ውድድሮች ተካሂደው አሸናፊዎች መለየታቸውም ተገልጿል።

ነገ በሚከፈተው የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ከ430 በላይ ቴክኖሎጂዎች ለኤግዚቢሽን እንደሚቀርቡም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

(በሔብሮን ዋልታው)