የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የቤጂንግ ሚሲዮን ከሻንሀይ፣ ጓንዦና ቾንቺን ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በቻይና የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል አክብረዋል፡፡
በቻይና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ስልጣኔና አኩሪ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፣ በታሪኳ ጎልተው ከሚታወቁና ከሚታወሱ በርካታ የታሪክ ሁነቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአድዋ ድል መሆኑን ተናግረዋል።
የአድዋ ድል የጣልያን ወራሪና ቅኝ ገዥን ኃይል ቅስም በመስበር የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበረ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ በዘረኝነት መንፈስ ላይ ተመስረቶ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችን በተለይም አፍሪካዉያንን በበታችነት ለዘላለም በቅኝ ለመግዛት አንደማይቻል አውሮፓውያንን ያስገነዘበም ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በአድዋ ዘመቻ ኢትዮጵያውያን ታላቅነታቸውን ያሳዩት በጦር ሜዳ ውሏቸው በሰሩት ጀብድ ብቻ ሳይሆን የጣልያንን እና ሌላውንም የአውሮፓ ሕዝብ ያስገረመው የጦር ምርኮኞች አያያዛቸውም መሆኑን አምባሳደር ተሾመ ጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻ በጓንዦ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር እውነቱ ብላታ መሪነት በቤጂንግ ሚሲዮን የትምህርት አታሼ ዕለቱንና ክብረ-በዓሉን አስመልክቶ የመነሻ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ከቻይና የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡