በጥምረት የሚካሄዱ የድጋፍ ስራዎች ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ፋይዳቸው ትልቅ ነው – ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ እና ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ

የካቲት 22/2013 (ዋልታ) – እንደ “ሰብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና መተከል” ያሉ  በጥምረት የሚካሄዱ የድጋፍ ተግባራት ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከ“ሰብዓዊነትና ፍቅር  ለትግራይና መተከል” የድጋፍ አንቅስቃሴ አስተባበሪና የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ በጥምረት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ መልካም እነደሆነና ይህን መሰሉ የድጋፍ ጥረቶች ኢትዮጵያዊነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ገልጸው ከጥምረቱ እንቅስቃሴዎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የመብት ተሟጋችና የድጋፉ አስተባበሪው ታማኝ በየነ “ፖለቲከኞች እና የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች ከህዝባዊ ሀላፊነታቸው ባሻገር ለህዝብ ችግሮች እንደ ዜጋ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው በውይይቱ ላይ ማንሳቱን በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከውይይቱ በኋላ የጥምረቱ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ እንዲቀጥል 50 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

“ሰብአዊነትና ፍቅር፣ ለትግራይና ለመተከል” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በነበረው ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋናና የእውቅና መርሃግብር በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል።