127 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ነሐሴ 2/2014 (ዋልታ) ባለፉት ስምንት ቀናት 127 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ከሐምሌ 21 እስከ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው የክትትል ዘመቻ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 14 ሰዎችንም በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተጠቀሱት ቀናት 127 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች ውስጥ 118 ነጥብ 5 ሚሊየን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች ሲሆኑ ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ደግሞ የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

በዚህም የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አቃቂ ቃሊቲ ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት ፣ እና ምያሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መሆናቸውን ከጉምሩክ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከልም አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡