2022 የዓለም ህዝብ በጦርነት እና በኑሮ ውድነት የተፈተነበት ዓመት

ታኅሣሥ 22/2015 (ዋልታ) የፈረንጆቹ 2022 አያሌ መልካምና መልካም ያልሆኑ ክስተቶች የተስተናገዱበት ዓመት ነበር፡፡ አገራት ወደ ጦርነት የገቡበት፣ ለጦርነት የቀረበ ፍጥጫዎች የተከሰቱበት እንዲሁም ስደት፣ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የተፈጠሩበት በአሉታዊ ጎኑ ይጠቀሳሉ፡፡ በአዎንታዊ ጎኑ ደግሞ ደግሞ የኮቪድ-19 ስርጭት መቀነስ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች እና ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት የተሰጠበት ዓመት ነበር፡፡ ባለፉት 12 ወራት የተከሰቱ አንኳር ጉዳዮች ዉስጥ ከብዙ በጥቂቶቹ እነሆ፡፡

  የሩሲያዩክሬን ጦርነት

የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት መንስኤው ውስብስብና አወዛጋቢ እንዲሁም በጊዜ ወደ ኋላ ብዙ የሚርቅ ቢሆንም የዩክሬን የሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ለመቀላቀል እንቅስቃሴ መጀመር ፈጣን መንስኤ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ገና ከጅምሩ ኔቶ እ.ኤ.አ በ1949 ሲቋቋም የቀድሞዋን ኮሙኒስት ሶቭየት ህብረት ወታደራዊ አቅም ለመገዳደር እንዲሆን ታቅዶ መመስረቱ እሙን ነው፡፡ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ስባሪ የሆነችው ዩክሬን የኔቶ አባል መሆን፣ ድርጅቱ የረቀቁ ጦር መሳርያዎችን ሩሲያ አፍንጫ ስር ለመትከል ያስችለዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሞስኮ በህልውናዋ ላይ የተቃጣ ከባድ አደጋ አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡ ይህ ዩክሬን ውሳኔ ለሩሲያ የህልውና አደጋ በመሆኑ “ምን ሲደረግ?” በሚል እ.ኤ.አ የካቲት 24/2022 ጦሯን ክተት ብላ የዩክሬን ግዛት ወረረች፡፡ ምዕራባውያንም ለዩክሬን ”አለንልሽ፣ ግፊ፣ በርች” እያሉ እርዳታውን ያጎርፉላት ጀመር፡፡ ለሩሲያ በግልጽ ድጋፍ ያደረገች ብቸኛ ሀገር ቤላሩስ ናት፡፡ በርግጥ ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በአደባባይ ባይደግፉም በዓለም መድረክ ሩሲያን ባለመቃወምና ከምእራቡ ዓለም ጋር ባለመተባበር ለሩሲያ በተዘዋዋሪ መንገድ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል፡፡ ለአስር ወራት የዘለቀው ጦርነት የበርካታ ሰዎችን  ህይወት ቀጥፏል፣ ብዙ ንብረትን አውድሟል፣ የዓለምን ኢኮኖሚም በአያሌው አዛብቷል፡፡ በዚህም የዓለም ምግብና ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡

   የቻይናአሜሪካ የከረረ ፍጥጫ

የቻይና – አሜሪካ ባላንጣነት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም እንደ ዘንድሮ ግን የከረረበት ወቅት ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ በ45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተከታታይ ማዕቀብና አጉራ ዘለል ውሳኔዎች የጀመረው ፍጥጫ በጆ ባይደን ዘመን የባሰ ከሮ ለግጭት ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ የፍጥጫው ጡዘት ደግሞ በነሐሴ 2022 መጀመሪያ የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ለመጎብኘት መወሰኗ ነበር፡፡ ታይዋን የግዛቴ አካል እንጂ ሉዓላዊ አገር አይደለችም የምትለው ቻይና የማንኛውም ሀገር መሪ ታይዋንን መጎብኘት ሉዓላዊነቷን እንደመጣስ ትቆጥረዋለች፡፡ በመሆኑም የፔሎሲ ጉብኝት የታይዋንን ሉዓላዊነት የሚያጸና የቻይናን ግዛት አንድነት አደጋ ላይ የጣለ  ነው በሚል ሁለቱ ኃያላን አገራት ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ያመራ ነበር፡፡ ሁለቱ ሀገራት በደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ የአየርና ባህር ኃይላቸውን በማስጠጋት ጡንቻ መለካካት ዳድቷቸው ነበር፡፡ ከፔሎሲ ጉብኝት በኋላ ግን 27 የቻይና ጦር አውሮፕላኖች የታይዋንን የአየር ክልል ጥሰው የገቡ ሲሆን ክስተቱ የዓለምን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

  የንግስት ኤሊዛቤጥ ሁለተኛ ሞት

እ.ኤ.አ ከ1952-2022 እንግሊዝንና 32 የጋራ ብልፅግና ሀገራትን በንግስትንት የመሩት ዳግማዊት ንግስት እልዛቤጥ በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በዚሁ 2022 ነበር፡፡ ንግስቲቷ በግዛት ዘመናቸው እንግሊዝን እየተፈራረቁ ከገዟት 15 ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ሰርተዋል፡፡ የ70 ዓመታት ንግስና ዘመናቸው ሐምሌ 8/2022 አብቅቶ ከዚህ ዓለም ሲለዩ ልጃቸው ልኡል ቻርልስ  በ73 ዓመቱ ንጉስ ተብሎ ተቀብቷል፡፡ በዚህም በእንግሊዝም ታሪክ በእድሜ ገፍቶ ንግስና የተቀባ ንጉስ አስብሎታል፡፡ በዘመናቸው 106 የዓለም ሀገራትን የጎበኙ ሲሆን ካናዳን 26 ጊዜ፣ አውስትራሊያን 18 ጊዜ እና ኒውዚላንድ ደግሞ 10 ጊዜ ጎብኝተዋል፡፡ በ1965 ኢትዮጵያን ለአንድ ሳምንት መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡ ሰፊ የሚድያ ሽፋን የተሰጠው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው፣ ቀብሩ ላይ የተገኙ የዓለም መሪዎች ብዛት እንዲሁም የጸረ-ዘውድ ተቃውሞ ሰልፎች ትኩረትን የሳቡ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

የዓለም ህዝብ ቁጥር 8 ቢሊዮን ማለፍ

2022 በዓለም ህዝብ  ቁጥር ወሳኝ ምዕራፍ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እ.ኤ.አ ኅዳር 15 ቀን 2022 የዓለም ህዝብ ቁጥር የ8 ቢሊዮን ወሰንን ያለፈበት ዓመት መሆኑ ነው፡፡ የዓለም ህዝብ ቁጥር በአንድ ቢሊዮን ለመጨመር የፈጀበት ጊዜ 11 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ ለዓለም ህዝብ ቁጥር መጨመር በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ያደጉት ሀገራት በተቃራኒው የውልደት ምጣኔያቸው በጣም ቀንሶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይነገራል፡፡ በህዝብ ብዛት ቻይና፣ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ኢነዶኔዢያ ፓኪስታንና ናይጀሪያ ከ1ኛ-6ኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡

የኳታር 2022 ዓለም ዋንጫ መስተንግዶ

የዓለም ሚጢጢዬዋ ሀገር ኳታር በዓለም እጅግ ተወዳጁን፣ ስኬታማውን ነገር ግን በዛው ልክ አወዛጋቢውን የዓለም ዋነጫን በአስደማሚ ብቃት የደገሰችው በዚሁ በ2022 ነበር፡፡ የአዘጋጅነት ሚናው የተሰጣት በእጅ መንሻ ነው በሚል ውንጀላ ጀመረው በ2010 ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ ኳታር ግን የዓለም ዋንጫ ዝግጅቷን ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጅዎች በመታገዝ 1.2 ሚሊዮን የኳስ አፍቃሪ እንግዶቿን ይህ ጎደለ ሳይባል ተንከባክባ ሸኝታለች፡፡ ቢቢሲ ከኳስ አፍቃሪያን  ባሰባሰበው ድምጽ፣ የኳታሩ ዓለም ዋንጫ በ78 በመቶ ድምጽ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ዓለም ዋንጫ ተብሎ ተመርጧል፡፡ የሊዮኔል ሜሲ ሀገር አርጀንቲናም የዋንጫው አሸናፊ ስትሆን ኳታር ለዝግጂቷም 229 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ከመላው የዓለም ህዝብ ስለራሷ መልካም ገፅታን ሸምታለች፡፡

የዝንጆሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ዳግም በዓለም ላይ መከሰት

ዓለም ከኮቪድ-19 ምስቅልቅል ተንፈስ ሳይል፣ ግንቦት 2022 የዝንጆሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ተከስቷል፡፡ ግንቦት 2022 መጀመሪያ አካባቢ በአሜሪካና አውሮፓ ሀገራት የተከሰተው በሽታው ለ252 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ላይ የተከሰተው እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ነበር፡፡ በበሽታው ከጥር 2022 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በ107 ሀገራት 82 ሺሕ 147 ሰዎችን አጥቅቷል ተብሏል፡፡

ኤለን መስክ ቲዊተርን መግዛት

በዚህ ዓመት በቴክኖሎጅው ዘርፍ ከተሰሙ ዓበይት ዜናዎች ውስጥ የኤለን መስክ ቲዊተርን መግዛት ዋነኛው ነበር፡፡ ደቡብ አፍሪካዊው ቢሊዬነር እና የቴስላ፣ ስፔስ ኤክስ እንዲሁም ኒዉራ-ሊንክ መስራች ኤለን መስክ ቲዊተርን ለመግዛት የማሰቡ ዜና መንሸራሸር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡  ድርጅቱን በ44 ቢሊዮን ዶላር የጠቀለለው ከብዙ ውዝግቦች በኋላ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ሚያዚያ 2022 ለመግዛት እንቅስቃሴ ቢጀምርም፣ በማህበራዊ ሚድያው ተጠቃሚዎች ቁጥር ዙሪያ ውዝግብ በመፈጠሩ የግዥው ሂደት እስከ ኅዳር 2022 ሊዘገይ ችሏል፡፡ ከግዥው በኋላም በርካታ አወዛጋቢ ዉሳኔዎችን በማህበራዊ ሚድያው በመለጠፍ ቲዊተር ተጠቃሚዎችን ቀልብ የሳበበት ወቅት ነበር፡፡ የቀድሞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሙዚቀኛውን ካኒያ ዌስት የታገዱባቸውን የቲዊተር አካውንቶች መልቀቁ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ኢራን ውስጥ የተቀሰቀሰዉ ተቃውሞ

በ2022 በርካታ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡ ከአሜሪካ እስከ ፈረንሳይ፣ ከጃፓን እስከ ሱዳን፣ ከሩሲያ እስከ ቦሊቪያ ታላላቅ ህዝባዊ ተቃውሞዎች በታላላቅ ከተሞች ተስተናግደዋል፡፡ የኢራኑ አመጽ ከነዚህ አንዱና እስካሁንም ያልበረደ ህዝባዊ ተቃውሞ ነው፡፡ መንስኤው የሲቪል ነጻነት ጥቄዎች በተለይ ደግሞ የሴቶች መብቶችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡  አመጹ መነሻ እ.ኤ.አ መስከረም 2022 ማህሻ ጅና አሚና የተባለች ሴት ፖሊስ የሚያስገድደውን አለባበስ ጥሳለች በሚል ከታሰረች ከሦስት ቀናት በኋላ የመሞቷ ዜና መሰማት ነበር፡፡ በሞቷ ዜና የተቀጣጠለው አመፅ በምዕራባውን ከፍተኛ የሚድያ ሽፋን የተሰጠው መሆኑ ከአመፁ በስተጀርባ የእነ አሜሪካ ስውር እጆች እንዳሉ ማሳያ ነው እየተባለ ነው፡፡ የኢራን መንግስትም ከ18 ሺሕ በላይ ሰዎችን አስሯል፤ 475 ሰዎች ሞተዋል፤ የሞት ቅጣት ከተላለፈባቸው ዜጎች ውስጥ ሁለቱ በስቅላት ተቀጥተዋል፡፡ 

የብራዚሉ የእግር ኳስ ፈርጥ ፔሌ ሞት

ፔሌ ወይም በመዝገብ ስሙ ኤድሰን አርናቴስ ዶ ናሴሜንቶ ዓለም ካፈራቻቸው አይረሴ እግር ኳሰ ተጨዋቾች አንዱ ነበር፡፡ በእግር ኳስ ህይወቱ ከአገሩ ብራዚል ጋር ሦስት ጊዜ የዓለምን ዋንጫ ያነሳው ፔሌ የኳስ ጥበቡን ለዓለም አሳቷል፡፡ ፔሌ በአንጀት ካንሰር ህመም ተይዞ በሳኦ ፖሎ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ82 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ተሰናብቷል፡፡ በኳታር ዓለም ዋንጫ ከተኛበት ሆስፒታል ሆኖ የአገሩን ልጆች፣ ሊዮኔል ሚሲን፣ ክሊያን ምባፔንና በአስገራሚዋ ሞረኮ ብቃት መደሰቱን በማህበራዊ ሚዲያ ከመግለፁም በላይ ፎቶዎቹን ሲያጋራ ነበር። የሞቱ ዜና እንደተሰማ የእግር ኳስ አፍቃሪያንና በርካታ የዓለም መሪዎች ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

የዓለም ህዝብ በዋጋ ግሽበት የተፈተነበት ዓመት

በዚህ ዓመት የዓለም ህዝብን ከፈተኑ ችግሮች መካከል ተጠቃሹ የዋጋ ግሽበበት ሲሆን አሁን አሮጌ ብለን ልንሸኘው የሰዓታት እድሜ በቀረው 2022 ዓመት መጀመሪያ ላይ ወትሮም በቋፍ ላይ የነበረው የሸቀጦች ዋጋ መናር በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ተባብሶ ጣሪያ የነካ ሲሆን በርካታ የዓለም ህዝብ የእለት ጉርሱን ሸምቶ ለመብላት በበርካታ ሀገራት ፈተና ውስጥ የገባበት ጊዜ ነበር፡፡

በ2022 የፈረንጆቹ ዓመት የዋጋ ንረቱ ዘጠኝ በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህ ደግሞ እያደጉ ያሉ ሀገራትን ብቻ ሳይሆን ያደጉ ሀገራት ዜጎችንም እጅጉን ፈትኗል፡፡ በአሜሪካ የፍጆታ እቃዎች ዋጋ ላይ ሰባት በመቶ የዋጋ ግሽበት ሲታይ ይህም ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ የተከሰተ ነው፡፡ በተመሳሳይ በጀርመንም አስር በመቶ የዋጋ ንረት የተመዘገበ ሲሆን በሀገሪቱ ባለ ሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ ከ1951 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተከሰተው፡፡

በቴዎድሮስ ሳህለ