በሆቴሎች ከሚሰሩ ውስጥ 23 በመቶ ብቻ ባለሙያዎች መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ሐምሌ 27/2008 (ዋኢማ)- በኢትዮጵያ ውስጥ በሆቴሎች እንዳስትሪ ከሚሰሩት ውስጥ 23 በመቶ ብቻ በሰለጠነ የሰው ሃይል እንደሚሰሩ የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሸብር ተክሌ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሆቴሎችና ቱሪዝም ሙያ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እያሉ በየቦታው የሚቀጠሩት 76 በመቶ በዘመድ አዝማድና በዕውቅና የሚፈጸም መሆኑ በጥናት መረጋጡን አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ ችግሩን ለማስወገድምና የሆቴል እንዳስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል ፍላጎትን ለማሳደግ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ በ2009 ዓመተ ምህረት ተግባራዊ ማድረግ ይጀምራል ብለዋል ፡፡

ፍኖተ ካርታው የማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩቱን የስልጠና ምርምርና የማማከር አገልግሎቱን በማላቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ለሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፍኖተ ካርታው ተቋማዊ ለውጥ በማምጣት ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ የአጭርና የረጅም ፕሮጀክቶችንና ፕሮግራሞችን በመዳሰስ ተግባራዊ ይሆናሉ ብለዋል ፡፡

በዚሁም ተቋሙ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል እንዲሆንና የላቀ ስልጠና፣ምርመርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያካሂድ እንደሚመረዳው አስገንዝበዋል ፡፡

በቀጣይም በሆቴሎች ያለው 23 በመቶ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ 80 በመቶ ከፍ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመተሳሰር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በ2017 ዓመተ ምህረት ደግሞ በአፍሪካ ከሚገኙ አምስት ቀዳሚ የሆቴልና ቱሪዝም መካከል አንዱ ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ፡፡

ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በሆቴልና ቱሪዝም ያሰለጠናቸውን 1ሺ 200 ተማሪዎች ሐምሌ 30/2008 ዓመተ ምህረት እንደሚያስመርቅ አስታውቀዋል ፡፡

ተቋሙ ስራ በጀመረበት በ1961 ዓመተ ምህረት የቅበላ ዓቅሙ 24 ሰልጣኞች ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 1ሺ 239 መድረሱን ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ዋልታ ዘግቧል፡፡