የከተሞች ፎረም “ የከተሞች ዘላቂ ልማትና የመልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን ” በሚል ቃል በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ የአስተዳደሩ ከንቲባ አስታወቁ ።
የከተሞች ፎረምን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ የሠጡት የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል እንደገለጹት፤ የጎንደር ከተማ 7ኛውን የከተሞች ፎረም ከሚያዚያ 21 እስከ ሚያዚያ 28/2009 ዓመተ ምህረት ለማካሄድ ዝግጅቶችን አጠናቃለች ።
ፎረሙ ከዚህ ቀደም በክልል ዋና ዋና ከተማዎች ሲካድ መቆየቱንና በክልል ከተማ በሆነችው ጎንደር ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው የጎንደር ከተማ ይህን እድል ያገኘችው ባለፈው ዓመት በተካሄደው የከተሞች ሳምንት አንደኛ በመውጣቷ ነው ብለዋል ።
እንደ ከንቲባው ገለጻ የጎንደር ከተማ የከተሞችን ፎረም በማዘጋጀቷ ያላትን የኢንቨስመንት ፣ የቱሪዝም፣ የባህል እምቅ ሃብት የተለያዩ የመልማት አቅሞቿን እንድታስተዋውቅ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላታል ።
በፎረሙ ላይ ከ200 በላይ ከተሞችና ከ20 በላይ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም ከ4 በላይ የሚሆኑ ከጎንደር ከተማ ጋር እህትማማችነትን የፈጠሩ ከተሞች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ።
ለሳምንት በሚቀየው የከተሞች ፎረም ላይ የተለያዩ አውደ ርዕዮች ፣ የፓናል ውይይቶች፣ የአልባበስና የአመጋገብ የባህል ትርኢቶች እንደሚካሄዱ የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ 20ሺ የሚሆኑ ዜጎች ይታደማሉ ተብሎ ተገምቷል ።
የከተሞች ፎረም መሪ ቃል “ የከተሞች ዘላቂ ልማትና የመልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን ” በሚል መሪ ቃል ” እንደሚካሄድ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።