ዘንድሮ ከመጋቢት 21 እስከ 28 2009 ዓ.ም በጎንደር ከተማ “የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን” በሚል መሪ ቃል ለ7ኛ ጊዜ የተከበረዉ የከተሞች ፎረም አዳዲስ ፈጠራዎች ይፋ የተደረጉበትና የተለያዩ አካላት ተሞክሮዎቻቸዉን ያጋሩበት እንደነበር የአማራ ክልል ከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ገለፁ፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ አቶ ሽቤ ክንዴ እንዳሉት የከተሞች ፎረም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በሃገር ደረጃ ሲከበር የቆየ ሲሆን ዓላማውም ከተሞች እርስበርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ጤናማ የዕድገት ውድድር እንዲያደርጉና ያላቸውን መልካም ተሞክሮ በመለዋወጥ ለከተሞች ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ እንደነበር አስታዉሰዋል፡፡
የዘንድሮውን ፎረም ያዘጋጁት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር፣የጎንደር ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ሲሆኑ በአጠቃላይ ከ200 በላይ ከተሞችና ከ10 በላይ አጋር አካላት እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከተሳታፊዎቹ 65 የሚሆኑት ከመሪ ማዘጋጃ ቤቶች ጀምሮ ከክልሉ የተመረጡ ከተሞች እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከባለፈው ጊዜ የሚለየው፣ በዓሉ ዓለማቀፋዊ ይዘት ያለውና ዓለማቀፋዊ እውቅና ያላቸው ልዑካን የተሳተፉበት መሆኑ ነው ያሉት አቶ ሽቤ፣ በዓሉ በሚከበርባቸው ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተለያዩ የፓናል ውይይቶች መካሄዳቸዉንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ የከተሞች ፎረም በክልል ዋና ከተሞች እስከ 6ኛው የከተሞች ፎረም ፕሮግራም ድረስ የተዘጋጀ ሲሆን ዘንድሮ የሚከበረው 7ኛው የከተሞች ፎረም ለመጀመሪያ ግዜ ከክልል ዋና ከተሞች ባለፈ መከበሩ ነው፡፡
የፎረሙ ታዳሚዎች በከተሞች ፎረም እየተሳተፉ የከተማዋን የኢንቨስትመንት አማራጮች በአካል የማረጋገጥ እድል እንዳገኙም አመልክተዋል፡፡ ከተማዋ የዞን ከተማ እንደመሆኗ መጠን በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ታሪክዊ ቦታዎች፣ የፋሲል አብያተ መንግስታት ፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፖርክ፣ የአልጣሽ ፖርክ እንዲሁም በአካባቢዋ የጀመረበት አጋጣሚ ስላለ በታሪክ አጋጣሚ ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት እድልም ተፈጥሯል፡፡
የከተሞች ልማት፣ዘላቂ ሰላምና መልካም አስተዳደር ለህዳሴአችን በሚል መሪ ቃል የተከበረው የከተሞች ፎረም የከተማዋን የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ በስራ እድል ፈጠራ፣ የመሰረተ ልማትና የመዝናኛ ቦታዎችን በማስፋፋት ሰፊ ዕድል እንደፈጠረም አቶ ሽቤ ተናግረዋል፡፡