የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ዕውን ለማድረግ በሚያስችል ዕድገት ላይ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ጥንቅር ድረሻ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማረጋጥ በሚያችል ቁመና ላይ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ፡፡

የ5ኛው የሕዝብ ተወካዮችና እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሶስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ዛሬ ሲከፈት የ2009ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም እንዲሁም የ2010 በጀት ዓመት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ የትኩረት ጉዳዮችን የሚዳስሱ ዝርዝር አቅጣጫዎች ፕሬዝዳንቱ ለምክር ቤቶቹ አቅርበዋል፡፡

አዲሱ ሚሌኒየም ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ሀገሪቷ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እንደሆነና በአማካይ 10 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት የተመዘገበ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. የ10 ነጥብ 9 የኢኮኖሚ ዕድገት እንደተመዘገበ ተጠቅሷል፡፡

የግብርናው ዘርፍ ምንም አንኳን በሀገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከዕቅዱ አንሶ ቢታይም በኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚያዊ ዕድግት ተመዝግቧል፡፡

በዚህም መሰረት የግብርናው ዘርፍ የ36 ነጥብ 3 በመቶ፣ ኢንዱሰትሪው የ25 ነጥብ 6፣ የማኑፋክቸሪንግ የ6 ነጥብ 4 እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ የ39 ነጥብ 3 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸውና ይህም የድርሻ ሽግሽግ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተስፋ በሚሰጥ የመዋቅራዊ ሽግሽግ ማድረግ መጀመሩን አመላካች እንደሆነ ዶከተር ሙላቱ ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም የ11 ነጥብ 1 የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ታቅዷል፡፡

በ2009 ዓ.ም. የተረጋጋ የማይክሮ ኢኮኖሚ ለመፍጠር በተደረገው ልዩ ትኩረት የዓመቱ ተንከባላይ የዋጋ ግሽበት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በነጠላ አሃዝ መገደብ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 7 ነጥብ 2 በመቶ ሆኖ ተመዘግቧል፡፡

ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ ከታቀደው 94 ነጥብ 3 በመቶ ያህል መሰብሰብ አንደተቻለና በተያዘው በጀት ዓመት የታክስ ሪፎርም ስራውን በተለይም የትልልቆቹን ታክስ ከፋዮች ላይ በማተኮር፣ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በጥናት የተመሰረተ ዘመናዊ አሰራርን በመከተል ውጤማ ሥራ ለማከናወን ታቅዷል፡፡

የኤክስፖርት ምርትና ግብይትም የሞት ሽረት ጉዳይ ተደርጎ እንደሚወሰድና ለሀገሪቷ ኤክስፖርት ገቢ 80 በመቶ ድርሻ ያላቸውን የቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም እንስሳት ንግድ ላይ በመጠንና በጥራት በመስራት ከፍተኛ ለውጥ ለመምጣት መታቀዱን ዶክተር ሙላቱ ገልፀዋል፡፡

በመዋቅራዊ ሽግግሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ በመሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ፣ የገናሌ3፣ የኮይሻ ግድብ፣ የመልካ ሰዲ ተርሚናል፣ የአሉቶ ጂኦተርማል፣ የረጲ ባዮማስ፣ የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች በዘንድሮው ዓመት ትኩረት ተሰጥቶባቸው የሚከናወኑ ፕሮጄክቶች እንደሆኑ ዋልታ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡