የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ መታገዱ ተገለጸ

ሚድሮክ የወርቅ አምራች የግል ኩባንያ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ በጊዜያዊነት መታገዱን የኢፌዴሪ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ኩባንያው በለገደምቢ በሚያካሂደው የወርቅ ማዕድን ልማት ስራ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የኩባንያው የምርት ሂደት የአካባቢ ብክለት እያስከተለ ነው የሚል ቅሬታ ማንሳታቸውን ተከትሎ  የኩባንያውን የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ በጊዜያዊነት  አግዷል።

በገለልተኛ አካል ጥልቀት ያለው ጥናት እስከሚጠና ድረስ የኩባንያው ወርቅ የማምረት ስራ መታገዱን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

ጥናቱ በገለልተኛ አካል ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮችን እና ባለ ድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ባጫ ፋጂ ለጋዜጠኞች ትናንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የኩባንያው ወርቅ የማምረት ሂደት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በጥናቱ ውጤት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ነው አቶ ባጫ የገለጹት።

አዲስ የሚከናወነው ጥናትም ጥልቀት ያለው እና በናሙና አወሳሰዱም ሰፊ እንደሚሆን ተገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመግለጫ እንዳስታወቀው  አዲስ የሚከናወነው የጥናት ውጤት ይፋ እስከሚሆን ድረስ ከግንቦት አንድ ጀምሮ የሚድሮክ ወርቅ የማምረት ፍቃድ በጊዜያዊነት ታግዷል፡፡