ኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የ3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስምምነት አደረጉ

የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የ3 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ስምምነት አድርገዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው።

በሁለቱ አገሮች መካከል ከተደረገው የ3 ቢሊዮን ዶላር ስምምነት ውስጥ 2 ቢሊዮኑ ኢንቨስትመንት ላይ የሚውል ሲሆን አንድ ቢሊዮኑ የባንክ ተቀማጭ እንደሚሆን ታውቋል።

የተደረገው ስምምነት ለአገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅር ሽግግር የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር በተለያዩ ሰባት ዘርፎች በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነት አድርጋለች።

ቱሪዝም፣ ዲፕሎማሲያዊ ቪዛ አገልግሎት፣ ኢኮኖሚያዊና ቴክኒካዊ ትብብር፣ እንዲሁም ባንክና ኢንቨስትመንት አገሮቹ በትብብር ለመስራት ከስምምነት የደረሱባቸው ጉዳዮች ናቸው።

አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አልናህያን በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው የስራ ጉብኝት ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ውጤት የተገኘበት መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል። (ኢዜአ)