የልማት ተነሺ አርሶአደሮችንተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች የመሰረተ ድንጋይ በየካ አባዶና ገላን ሳይት ተቀመጠ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ደሪባ ኩማ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ነው   በዛሬው  ዕለት  የመሠረተ ድንጋዮቹ የተቀመጡት ።

ፕሮጀክቶቹ በልማት  ለሚነሱ  አርሶ አደሮች አገልግሎት  የሚሠጡ  የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት ቤት እና መሰል የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት የሚያስችሉ ሲሆን በአጠቃላይ 500 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በተለይም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን  በሚቀጥሉት ሶስት እና አራት ወራት በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ይገባሉ  ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚሁ የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ስነስርዓት ንግግር ያደረጉት ከንተባ ድሪባ ኩማ እንደገለጹት ዜጎች ሥርዓት ባለው መልኩ ባለመስተናገዳቸው ምክንያት  ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የደረሰባቸውን የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ አስተዳደሩ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዞ በርካታ አርሶአደሮች የተፈናቀሉ መሆኑን ጠቅሰው ወደ አርሶአደሮች ቀድሞ ህይወታቸው እንዲመለሱ የክልሉ መንግስት ይሰራል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡