ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችል ብሄራዊ መርሐ-ግብር አስጀመሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያን የንግድና የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ለማሻሻል የሚያስችል ብሄራዊ መርሃ-ግብር አስጀምረዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ የስራ ፈጠራ መርሃ-ግብር አካል ሲሆን ንግድን ለመጀመርና ለማሳደግ ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት ይጨምራል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ የሥራ ፈጠራ እድገት እንደሚያስፈልግና በማደግ ላይ ያለ ጠንካራ የግል ዘርፍ ለሥራ ፈጠራ አጀንዳ ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል፡፡  

መንግስት የግሉን ዘርፍ ከማደግ እና የሥራ ዕድል እንዳይፈጥር የሚያግዱ እንቅፋቶችን ለይቶ በማውጣት ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡

ብሄራዊ መርሃ-ግብሩም በ10 አስፈፃሚ ተቋማት የሚተገበሩ 80 ልዩ ተግባራትን መያዙ ተገልጿል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቆጣጣሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፖሊሲና አፈፃፀም ክፍል ክትትል እየተደረገበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚያስተባብረው ይሆናልም የተባለው፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)