ኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነዉ

ከ47 አገራት በተዉጣጡ ተሳታፊዎች እየተከበረ የሚገኘዉ ኢኖቬት ኢትዮጵያ ሳምንት አንዱ መርሃ ግብር የሆነዉ ኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ ዛሬ በሸራተን ሆቴል በማካሄድ ላይ ነዉ፡፡

በጉባኤዉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ደረጃ ከቴክኒክ መሰረተ ልማት አንፃር የተሻለ ቢሆንም ከዜጎች ተጠቃሚነት አኳያ ግን ዉስንነቶች እንዳሉባት ተናግረዋል፡፡

ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠትና በተለይ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ይበልጥ በማተኮር ክፍተቱን ለመሙላት መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት ኮመንዌልዝ የአይቲዩ ቡድን ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ባሻር ጋዋንዶ በበኩለቸዉ በአፍሪካ በየአመቱ ከ75 ቢሊየን ዶላር በላይ በዲጂታል ቴከኖሎጂ እንደሚንቀሳቀስ ጠቁመዉ ዘርፉ የሚጠይቀዉን መሰረተ ልማት ይበልጥ በማሟላት ለአህጉሩ ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረዉን ድርሻ ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂ በአፍሪካ በየአመቱ 20 በመቶ እድገት እያሳየ ሲሆን አብዛኛዉ ተጠቃሚዎቹ ከ24 ዓመት በታች የሆኑ እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡

በአፍሪካ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት 22 በመቶ ብቻ ሲሆን ተደራሽነቱም ገና 6 በመቶ ነዉ፡፡

ቴክኖሎጂዉን በመጠቀም ናይጀሪያና ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚዉን ስፍራ ይይዛሉ፡፡