ኢትዮጵያን ደቡብ ኮሪያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ ገለፁ

ሁለቱ አገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመቀነስና  አካባቢ ጥበቃ ስራን ለማጠናከር የተለያዩ ልምዶች የሚገኙበት የጋራ መድረክ አዘጋጅተዋል::

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለዉጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍቃዱ በየነ ኢትዮጵያ እየገነባች ላለዉ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የካርበን ልቀትን መቀነስ አንዱ አጀንዳ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዚህም ኮሪያ የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ሆን ሚን ሊም የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም አለምአቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያና ኮሪያም በጋራ እንደሚሰሩና የኮሪያ ተሞክሮም ለኢትዮጵያ እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለዉጥ ላይ ያተኮረ የኮሪያ ተሞክሮ በኮሪያ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለኢትዮጵያ የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እየተሰጠ ነዉ፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመቋቋም ከኮሪያ አለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር እየሰራች ትገኛለች፡፡

የአየር ንብረት ለዉጥ እያስከተለ ያለዉን ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችል የተሞከሮና ልምድ ልዉዉጥ በኢትዮጵያና ደቡብ ኮሪያ መካከል እየተደረገ ነዉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የአቅም ግንባታና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ የፓሪሱን የአየር ንብረት ለዉጥ ስምምነት ከፈረሙ አገሮች አንዷ ናት፡፡ በዚህም ስምምነቱን በማክበር ለሌሎች አገራት ምሳሌ ለመሆን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ እያከናወነች ትገኛለች ተብሏል፡፡