አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የቻይና ቴን ጄን ከተማ የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ, ጥቅምት 29 ቀን 2004 (ዋኢማ) – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የቻይና ቴን ጄን ከተማ የልዑካን ቡድን አባላትን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የልዑካን ቡድኑ መሪ ሚስተር ዢንግ ዩዋሚን እንዳሉት ቻይና በአቅም ግንባታው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ለማድረግ የኢትዮ-ቻይና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ የማስቀጠል ፍላጎት አላት፡፡

እንዲሁም ለኮሌጁ የ5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ለአፈ ጉባዔ አባዱላ ገልፀውላቸዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ የቴን ጄን ከተማ ከአዲስ አበባ እንዲሁም የቴንጄን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር የእህትማማች ግንኙነት እንዲፈጥሩ እንደሚሹ ገልፀዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ በበኩላቸው ቻይና በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ እያደረገች ያለው ድጋፍ ሀገሪቱ ያለባትን ውሱንነት ለመቅረፍ የጀመረችውን የአቅም ግንባታ ተግባር ያቀላጥፋል፡፡

የቴንጄን ከተማ እና የቴን ጄን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ያቀረቡትን የእህትማማች ጥያቄም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚደግፈው ለልዑካን ቡድኑ ገልፀዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ 50 ላፕቶፕ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስጦታ አበርክቷል፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የቴን ጄን ከተማን እንዲጉበኙም የልዑካን ቡድኑ ግብዣ አቅርበውላቸዋል፡፡