በግብርናና በኢንዱስትሪ መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ736 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ግዥለመፈጸም ቃል ገቡ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2004/ዋኢማ/ – ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በግብርናና በኢንዱስትሪ የስራ መስኮች የተሰማሩ ባለሃብቶች ከ736 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ግዥ ለመፈጸም ቃል ገቡ።

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዥ ለመፈፀም ቃል ለገቡ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች በሂልተን ሆቴል የምስጋና ፕሮግራም ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስቴርና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት በዚህ ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው በግብርና መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከ469 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም በኢንዱስትሪው መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ደግሞ ከ266 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ በድምሩ ከ736 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የቦንድ ግዥ ለማከናወን ቃል ገብተዋል።

በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ለባለሃብቶቹ የምስጋና የምስክር ወረቀት የሰጡት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ በረከት ስምኦን መንግስት በማኑፋክቸሪንግና በግብርና መስኮች ለተሰማሩ ባለሃብቶች አመቺ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

መንግስት ከባለሃብቶቹ ለልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የዘርፉ ተዋንያን የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች ለመፍታትም የላቀ ጥረት እንደሚያደርግ ያረጋገጡ ሲሆን፤ ባለሃብቶቹ መንግስት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ለሰጡት ፈጣን ምላሽም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መኮንን ማንያዘዋል በበኩላቸው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር እንዲሆን ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸው፤ መጪው ጊዜ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ብሩህ መሆኑን ጠቁመዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅም በኢንዱስትሪው መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከሌላው በተሻለ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በበኩላቸው፤ ባለፉት ስምንት ተከታታይ አመታት በግብርና መስክ በአማካኝ ከ8 በመቶ በላይ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በእድገትና ትርንስፎርሜሽን እቅዱም የግብርና ዘርፍ እድገቱ በላቀ ሁኔታ እንዲቀጥል ሁሉን አቀፍ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ዜጎች ለግድቡ ግንባታ ስኬት እያደረጉ ያሉት ድጋፍም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት ባለሃብቶች በቡና ልማት ዘርፍ፣ በጥጥ ልማት፣ በሜካናይዜሽንና በምግብ ሰብል ምርት፣ በቁም እንስሳት ንግድ፣ ስጋና የስጋ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ፣ በኬሚካል ማምረትና ማስመጣት የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሃብቶች መሆናቸውን ኢዜአ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
ዋኢማ