በአቢዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ግዴታውን በሚገባ እየተወጣ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2004/ዋኢማ/ – በአቢዬ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ግዴታውን በሚገባ እየተወጣ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመስክ ድጋፍ ሰጪ ክፍል ምክትል ዋና ፀሐፊ ሚስ ሱዛና ማልኮራ ገለጹ፡፡ ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድጋፍ ሰጪ ክፍል ዋና ፀሐፊ ሚስ ሱዛና ማልኮራ ጋር ትናንት በጽህፈት ቤታቸው በጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ሚስ ሱዛና እንደገለጹት፤ ሰሞኑን በአቢዬ ተገኝተው ባደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል የተጣለበትን ግዴታ በሚገባ እየተወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በዚህም የተሰማቸውን ደስታ ለአቶ ሃይለማርያም በመግለጽ ለኢትዮጵያ መንግስት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀጣይም ለሰላም አስከባሪ ሃይሉ የሚያስፈልገው የሎጀስቲክ ድጋፍ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ የሰላም አስከባሪ ሃይሉ የተጣለበትን ግዴታ በሚገባ እንደሚወጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አብሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የኢጋድ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በሱዳን የተከሰተውን ችግር መፍትሄ ለመሻት መወያየት ጥሩ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል በጉዳዩ ላይ በተወያዩበት ወቅት መግለጹቸውን ውይይቱን የተከታተሉ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡