አዲስ አባባ፤ ህዳር 7/2004 (ዋኢማ) – በዳውሮ ዞን ተርጫ ከተማ ራሱን በእሳት ለኩሶ የገደለው የኔሰው ገብሬ በነበረበት ከፍተኛ የአዕምሮ ህመም መሆኑን የሟች ቤተሰቦችና የአካባቢው ነዋሪዎች አረጋገጡ።
የተለያዩ ሚዲያዎች የሟች የኔሰው ገብሬ አሟሟትን የሚመለከት ሃሰተኛ ዘገባዎች ማሰራጨታቸውን ተከትሎ የዋልታ የኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋዜጠኛ ጉዳቱን በቅርበት ከሚያውቁ ከሟች ቤተሰቦች፣ ከተርጫ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የዳውሮ ዞን ፖሊስ አዛዥና ከዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ሟች ራሱን ያጠፋው በነበረበት የአእምሮ ህመም ምክንያት እንጂ ምንም አይነት የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ጋር ግንኙነት እንደሌለው አረጋግጠዋል።
የተርጫ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መብራቱ ማሴቦ ስለ ሟች የጤና ሁኔታ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የኔሰው ገብሬ በህይወት ባለበት ጊዜ ከፍተኛ የአእምሮ መታወክ እንደነበረበትና ለዚህም የተለያዩ መድሀኒቶችን ይጠቀም ነበር።
ሟች በሆስፒታሉ በተለያየ ጊዜያት የአእምሮ ህክምና ሲያደርግ መቆየቱን በሆስፒታሉ ያሉ የህክምና ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱ የጠቆሙት አቶ መብራቱ፣ ሟች በራሱ ላይ የእሳት አደጋ ካደረሰ በኋላ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ድጋፍ ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱንና የህክምና እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ ህዳር 4/2004 አመተ ምህረት ህይወቱ ማለፉን አስረድተዋል።
ወይዘሮ ታደለች በቀለ ይባላሉ የተርጫ ከተማ ነዋሪና የሟች የኔሰው ገብሬ ታላቅ እህት፣ ከአቶ የኔሰው ጋር ያላቸውን ዝምድና፣ ሟች በህይወት ሳለ ነበረበት ስለተባለው የአእምሮ መታወክ ህመምና አሟሟቱን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ አቶ የኔሰው የእናታቸው ልጅ ሲሆን የወይዘሮ ታደለች ሁለተኛ ታናሽ ወንድም እንደሆነም ተናግረዋል።
አቶ የኔሰው ከአዋሳ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት ከተመረቀ በኋላ በስልጤ ዞን ለጥቂት ወራት እንዳስተማረና ከዛም በነበረበት የአእምሮ መታወክ ምክንያት ስራ ለቆ ወደ ተርጫ እንደተመለሰ ቀጥሎም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በጤናው ላይ የተወሰነ ለውጥ ሲመጣ በተርጫ ቴክኒክ ትምህርት ቤት ለሰባት ወራት ሲያስተምር መቆየቱን፤ ሟች በነበረበት የአእምሮ ጤንነት ችግር ስራውን እንደለቀቀ አስረድተዋል።
“ወንድሜ በህይወት ሳለ የጫት፣ የሲጋራና የመጠጥ ሱስ ስለነበረት ገንዘብ አምጪ እያለ ያስቸግረኝ ነበር። ሲጠጣ ደግሞ እኔንና ቤተሰቤን ብሎም የአካባቢውን ሰዎች እየረበሸ ስላስቸገረኝ በ2001 አመተ ምህረት ፖሊስ ይዞልኝ እንዲታሰር አመልክቻሁ። ነገር ግን ከአቅሜ በላይ መሆኑንና መጨከኔን ሲረዳ ከአካባቢው ርቆ ለሁለት አመታት ቆይቶ ነበር።” በማለት ወይዘሮ ታደለች ገልጸዋል።
ወይዘሮ ታደለች አክለውም “መስከረም መጀመሪያ አካባቢ ወደ ተርጫ ተመልሶ መጣ። ከዛም ጥቅምት አጋማሽ ጀምሮ ህመሙ እየበረታበት ሄዶ እኔንና ቤተሰቤን ማወክ ቀጠለ እኔም ባለፈው ሳምንት በ2001 ያስገባሁትን ክስ ለማንቀሳቀስ በዝግጅት ላይ ሳለሁ ነው እንግዲህ ይህ አደጋ የተፈጠረው።” ሲሉ ተናግረዋል።
በሟች የኔሰው ገብሬ አሟሟት የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱ ሰዎች መጠቀሚያ መሆኑ እንዳንገበገባቸው የሚገልጹት ወይዘሮዋ በተለይ በቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራምና ኢሳት በተባለው የሬዲዮ ፕሮግራም የተሰራጨው ፍጹም ከእውነት የራቀ ዘገባ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ታደለች ገለጻ ከሟች ቤተሰቦች ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ በቤተክርስቲያን ስነ ስርአት በክብርና በህዝብ ታጅቦ የተከናወነውን የቀብር ስነ-ስርዓት በሀሰት ዘገባ የወንድማቸውን ስም ባጠፉ የመገናኛ ብዙሃን ሃፍረት እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የዳውሮ ዞን ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ምክትል ኮማንደር ባኮ ቲና በበኩላቸው ሟች በተርጫ አካባቢ የአምሮ ችግር እንዳለበት እንደሚታወቅና የሟች እህትም በዚሁ ምክንያት ለፖሊስ ከዚህ ቀደም ማመልከታቸውን አስታውሰዋል።
በሟች የቀብር ሁኔታ የተሰራጨው ዘገባ ፈጽሞ ሃሰት መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮማንደሩ፤ የሟች ቤተሰቦች ጅማ እንደሚኖሩና ዋካ አካባቢም ምንም አይነት ቤተሰብ የሌላቸው ሲሆን አስክሬኑንም ወደዋካ ለመውሰድ ፍላጎት አለመኖሩን አመልክተዋል።
ሟች በደረሰበት አደጋ ሆስፒታል ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቹ ሲያስታምሙት መቆየታቸውን የገለጹት ምክትል ኮማንደር ባኮ፣ በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይም ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን የቀብር ስነ-ስርዓት መከናወኑን አስረድተዋል።
የተርጫ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እስራኤ አታራ በበኩላቸው፤ በሟች የኔሰው የአሟሟት ሁኔታ በተለይ በቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራምና ኢሳት በተሰኘው የሬድዮ ፕሮግራም ላይ የተሰራጨው ዘገባ ሚዛናዊነት የጎደለውና ፍጹም የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ መሆኑን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ተናግረዋል።
የዋካ አካባቢ ነዋሪዎች የዞኑን ከተማ ከተርጫ ወደ ዋካ እንዲዛወር ባቀረቡት ጥያቄ ውስጥ አቶ የኔሰው ምንም አይነት ተሳትፎ እንዳልነበረው ተናግረው፤ ግለሰቡ በአእምሮ ህመም እንደሚሰቃይ የተርጫ አካባቢ ነዋሪዎች እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
የሟች የኔሰው ገብሬ የአሟሟት እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያ ውስጥ አመጽና ሽብርተኝነትን ለማስፋፋት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖች የተዛባና የሀሰት ዘገባዎችን በማሰራጨት በህዝቡ ላይ ውዥንብር ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ዋጋ እንደሌለው መረዳት ይቻላል።
በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያን ህዝብ ለአመጽ የሚቀሰቅስ ጥሪ ሲያቀርቡ ህዝቡ በበኩሉ ጆሮውንም ልቡንም ስለነፈጋቸው የሟች የኔሰውን አሟሟት ከቱኒዚያው ወጣት ጋር ለማመሳሰል ያደረጉት ጥረት ቀቢጸ ተስፋቸውን እውን ለማድረግ የተጠቀሙት ዘዴ መሆኑን ማንም መረዳት አያዳግተውም።
በመላው አለም የተከሰተውን የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና በተለይ በአረቡ ሀገራት ለዘመናት ስር ሰዶ የቆየውን ንጉሳዊ ስርዓትና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ከሚቃወሙ ህዝቦች ጋር ኢትዮጵያን ማመሳሰል አላዋቂነትና ሀገሪቱም እንዲህ ያለውን የእርስ-በርስ ግጭት ከ20 አመታት በፊት እንዳለፈችው ያለመረዳት ውጤት ነው።
በመጨረሻም ሰለጠኑ የተባሉት ሀገራት ሳይቀር በኢኮኖሚ ቀውስ ሲንገዳገዱ ኢትዮጵያ በያዘችው ልማታዊ አቅጣጫ የዓለም ሀገራት የሚመሰክሩት ፈጣን እድገት ማስመዝገቧ መንግስትና ህዝብ ለልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚዘክር ነው።
ይህ ሆኖ ሳለ ለርካሽ ፖለቲካ ጠቀሜታ ሲሉ እውነትነትን የሌለውን መረጃ በማሰራጨት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የተረጋጋ ፖለቲካ ለማደፍረስ የሚፈልጉ በውጭ ያሉ ሚዲያዎች በተለይም ኢሳትና ቪኦኤ ከእንደዚህ አይነት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የሟች ቤተሰቦች መግለፃቸውን ዋልታ የኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።