አዲስ አበባ, ህዳር 15 ቀን 2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ በሶማሊያ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዛሬ ማምሻውን በጽሕፈት ቤታቸው የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አሕመድን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት በሶማሊያ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥ የሚያድረጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የሁለቱ አገራት የጋራ ጠላት የሆነውን አልሸባብን ለማዳከም በጋራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በሽብር ድርጊት የሚያምሰው አልሸባብን ለማስወገድ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ የሽግግር መንግሥትና ከኢጋድ አባል አገራት ጋር ወደፊትም ተባብራ እንደምትሰራ አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያ ቋሚ መንግሥት እንዲመሰረት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አሕመድ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ወንድማማችነትና ትብብር ከመቼውም በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በተለይ አሸባሪውን የአልሸባብ ቡድን የሽብር ድርጊት ለመግታት ኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ተጠክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለው ድጋፍ በሶማሊያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
ሼክ ሸሪፍ ነገ በሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት ዛሬ ከቀትር በኋላ ነው፡፡ (ኢዜአ)