የኢህአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የገጠርና የከተማ ሥራዎችን በመገምገምና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3 ቀን 2004 /ዋኢማ/ – የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን ስድስት ወራት የገጠርና የከተማ ሥራዎች ዕቅድ በመገምገምና ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ በገጠር በተደራጀ የሕዝብ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ አበረታች መሆኑን ገምግሟል።

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በትግራይ ክልል  ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ለማካሄድ በዕቅድ ዝግጅት፣ፈጻሚ አካላትን በማዘጋጀትና በአፈጻጸም ረገድ የተደረገው እንቅስቃሴ ለሌሎች ክልሎችአስተማሪ መሆኑ ተመልክቷል። በሌሎች ክልሎች በተደራጀ የሕዝብ እንቅስቃሴ መልክ ለመምራት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክር ቤቱ አስገንዝቧል።

በተጨማሪም በገጠር የሕዝቡ ተሳትፎ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባሻገር፤ በመስኖና በሰብል ልማት እንዲሁም በሌሎች የገጠር የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎች ላይም ተግባራዊ እንዲደረግ ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቷል።

በአርሶ አደሩ የተጀመረው የተደራጀ እንቅስቃሴ እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢያንስ አንድ የውሃ አሰባሰብ አማራጭ ተጠቃሚ እንዲሆን የዝናብ እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ የምርት መስተጓጎል ሳያስከትል ለመቋቋም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ምክር ቤቱ የገጠር የበጋ ወራት ሥራዎችን በማጠቃለል ለክረምት ሥራዎች ዝግጅት ከወዲሁ እንዲጀመርና ሥራዎቹን በተሟላ የሕዝብ ንቅናቄ ለመምራት ክልሎቹ ከበጋው እንቅስቃሴ ልምዶች በመነሳት በየደረጃው ፈጻሚውን የማብቃት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስቧል።

በከተሞች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ለማደራጀት፣የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ፣የንግድና የግብር ሥርዓቱን ለማሻሻል፣የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱን መልክ ለማስያዝ ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝቧል።

ከዚሁ በተጓዳኝ በተለያዩ መስኮች የሚታየውን አለአግባብ የመጠቀም አመለካከትና ተግባር ለመታገል የሕዝቡን ተሳትፎ መሠረት በማድረግ እንቅስቃሴ መደረጉ የተመለከተ ሲሆን፣ የሥራዎቹ አበረታችነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአፈጻጸም ሂደት በተለይ ለሕዝቡ ተገቢውን መረጃ በመስጠትና ተሳትፎውንም በማጎልበት ረገድ እስካሁን ከተከናወነው በላይ መሰራት እንዳለበት ወስኗል።

በተለይም ሥራዎችን በተጠናከረ የሕዝብ ተሳትፎ ለማከናወን የተጀመረው ሥራ ከዝግጅት አንጻር አመርቂ ቢሆንም፤ አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት ጥረት እንዲደረግ አሳስቧል።

ምክር ቤቱ በከተሞች የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎች አማካኝነት የሚደረገው ጥረት እንዲቀጥልና በተለይ እንደ ስኳር፣ዘይትና ስንዴ ያሉት መሠረታዊየፍጆታ ሸቀጦችን መንግሥት በስፋት በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል።

በከተሞች የተጀመረውን የሥራ ፈጠራ እንቅስቃሴ በተጠናከረ መንገድ በማስቀጠል የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት መረባረብ እንደሚገባም ምክር ቤቱ አስገንዝቧል።

በሌላ በኩል የኢህአዴግ ምክር ቤት በቅርቡ በአገሪቱ የእስልምና ሃይማኖትን በማስታከክ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በዝርዝር የገመገመ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባና መንግሥትም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ፤ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩል የመታየት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸውና መንግሥታዊ ሃይማኖት የሚባል ነገር እንደማይኖር ምክር ቤቱ አስታውሶ፣አንዳንድ ኃይሎች የማተራመስ ዓላማቸውን ለመጠቀም የሚያደርጉትን ጥረት ሕዝበ ሙስሊሙ በተረጋጋ መንፈስ እውነቱን ለማወቅ ያደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶታል።

ሕገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር የሁሉም ዜጎች ግዴታ በመሆኑ በቀጣይም ችግሮችን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዜጎች እንዲንቀሳቀሱ አሳስቧል። እስካሁን ድረስ መንግሥት ያደረገው እንቅስቃሴ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ማድረጉን የገመገመ ሲሆን፣ ማንኛውም ቀጣይ የመፍትሄ እንቅስቃሴም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ማድረግ እንደሚገባው አቅጣጫ አስቀምጧል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም በየደረጃው ያለውን አመራር የሚያጠናክሩ የግምገማና ሌሎች የማስተካከያ እንቅስቃሴዎች ከሕዝቡ ተሳትፎ ጋር ተሳስረው የተጀመረውን ልማት በሚያፋጥንና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚያስወግድ አግባብ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባው መጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።