የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል በኢትዮ ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር በሚገኙ የሽብርተኛ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 7/2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል በኢትዮ-ኤርትራ አዋሳኝ ድንበር በሚገኙ የሽብርተኛ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ በወሰደው እርምጃ በቦታው በነበሩ የሽብርና የጥፋት ሃይሎች ላይ ተመጣጣኝ ጥቃት እንዳደረሰ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ለዋልታ በላከው መግለጫ እንደገለጸው በትናንትናው እለት ከኢትዮጵያ የአፋር ክልል አዋሳኝ ድንበር ከ14 እስከ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የፀረ ኢትዮጵያ ተላላኪ ሃይሎች ወታደራዊ ስልጠና ማእከላት በሆኑት ራሚድ፣ ገላህቤንና ጊምቢ በነበሩ የጥፋት ሃይሎች ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል በወሰደው ተመጣጣኝ ጥቃት የሽብር ሃይሎችን ማጥቃቱን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል  ግዳጁን በስኬት ፈፅሞ ወደ መደበኛ ካምፑ መመለሱን የገለጸው መግለጫው  ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ውዝግብ በሰላምና በድርድር ሊፈታ እንደሚችልና እንደሚገባ በማመን ተደጋጋሚ የሰላም ሃሳብ ማቅረቧን ጠቁሟል፡፡

መግለጫው አክሎም ኢትዮጵታ  በሁለቱ ተጎራባች አገሮች መካከል ያለውን አለመግባባት በድርድር ይፈታ ዘንድ በየትኛውም  ቦታና ጊዜ ከኤርትራ መንግስት ጋር በማንኛውም ጊዜ ለመወያየት ዝግጁ መሆኗንም  ገልጿል፡፡

የኤርትራ መንግስት ለዚህ የሰላም ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ሰላምንና ፀጥታን ለማናጋት ከተንቀሳቀሰ ግን ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ አፀፋዊ እርምጃ   እንደሚትወስድ  መግለጫው አስታውቋል፡፡

የኤርትራ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ የሽብርና የማተራመስ ስትራቴጂን እንደ ስልት  እየተከተለ የተለያዩ ፀረ ሰላምና ጠብ ጫሪ ድርጊቶችን በመፈፀም ላይ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ “ሰላምና መረጋጋት የለም” የሚል ምስል ለመፍጠርና ጉባኤውን ለማሰናክል ፀረ ሰላም የሆኑ የኢትዮጵያ ተላላኪዎችን በመጠቀም አዲስ አበባ ውስጥ ለመፈፀም ያሴረው የሽብር ድርጊት ሳይሳካ መክሸፉንም አስታውሷል፡፡

“አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ” በሚል መርህ ወታደራዊ ስልጠና ሰጥቶና አስታጥቆ ወደ አገር ውስጥ የላካቸው እነዚህ የፀረ ሰላምና የሽብር ተላላኪዎች ሊፈፀሙት የነበረው የሽብር ጥቃት ቆይቶ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራና የሶማሊያ ሁኔታ አጣሪ ቡድን ባካሄደው ጥናት ጭምር መረጋገጡንም መግለጫው ያስረዳል፡፡

መግለጫው አያይዞም በዚህ አመትም  በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ የኤርትራ መንግስት ፀረ ሰላም ተላላኪ ሃይሎችን በመጠቀም በቅርቡ በአፋር ክልል በጉብኝት ላይ በነበሩ ቱሪስቶች ላይ በወሰደው የሽብር ጥቃት አምስት ቱሪስቶች ተገድለው ሌሎች መታገታቸውን ጠቁሟል፡፡

የኤርትራ መንግስት እየፈጸመ ያለው የሽብርተኝነት  ተግባር ዋና አላማ በኢትዮጵያንና  በአፍሪካ ቀንድን አለመረጋጋትን ለማስፈን መሆኑን መግለጫው ገልጿል፡፡

የሽብር ጥቃቱ በተፈፀመበት ሰሞን የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስት ከዚህ መሰል የሽብርና የፀረ ሰላም ተግባሩ የማይታቀብ ከሆነ ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ራሷን እንደምትከላከል አስታውቆ እንደነበርም መግለጫው አስታውሷል፡፡