በባሌ ዞን የጊኒር ወረዳ ሰራተኞች ለህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤  ሐምሌ 8/2005 (ዋኢማ) – በባሌ ዞን የጊኒር ወረዳ የመንግስት ሠራተኞች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እስከሚጀምር ድጋፋቸዉን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ።

በወረዳው ከመንግስት ሠራተኞች በተጨማሪ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ2 ነጥብ 4ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የቦንድ ግዥ የፈጸሙበትን ማረጋገጫ ሰነድ በተቀበሉበት ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት እስኪጀምር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።

የወረዳው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጸሃይ አለሙ እንደገለጡት የወረዳው የመንግስት ሠራተኞች በአንድ ወር ደሞዛቸው ቦንድ በመግዛት ከ1ሚሊዮን 800 ሺህ ብር በላይ ገቢ አድርገዋል። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልጀዋድ ሀሰን በበኩላቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሚሰጠው የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባሻገር የመንግስት ሠራተኛው የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድግ ያደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ኢዜአ እንደዘገበው በወረዳው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ2 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ መግዛታቸውንና በቀጣይም ግድቡን በራሰችን ገቢ ብቻ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የተለያየ መርሃ ግብሮችን አውጥተው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።