የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በባህር ዳር ከተማ ተጀመረ

ባህር ዳር ፤ ጥር 17/2006 (ዋኢማ) – በልማት የበለፀገችና የተዋህደች አፍሪካን ለመፍጠርና የኢኮኖሚ እድገት ህዳሴዋን ለማረጋገጥ የአፍሪካ ህብረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስገነዘቡ።
ትላንት ማምሻውን በባህር ዳር ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪካ ህብረት የምክክር መድረክ ዛሬ ሲጀመር ሚኒስትሩ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንደገለፁት አፍሪካ የሰላምና የልማት ቀጠና እንድትሆን የተቀናጀ ስራ መከናወን አለበት።
አፍሪካ ከፀጥታ ስጋት ነፃ ሆና ለዜጎቿ ምቹ መኖሪያና በልማት የበለጸገች አህጉር እንድትሆን የአፍሪካ መሪዎች ሰፊ የእድገት እቅድ ይዘው በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባም ገልፀዋል።
አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው አቅም የመፍታት ልምዳቸውን በማሳደግ በእውቀት ላይ የተመሰረተና ሊተገበሩ የሚችሉ የጋራ እቅዶችን በመንደፍ ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለመጭው ትውልድ ለምለምና ለኑሮ ምቹ የሆነች አፍሪካን ለማስረከብ  የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ዱላሚኒ ዙማ በበኩላቸው አፍሪካ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ ባለፉት 50 ዓመታት ካጋጠሟት ችግሮች ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ሃምሳ ዓመታት የበለፀገች አህጉር ለማድረግ አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫም ምክር ቤቱ በሁለት ቀን ቆይታው በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፀጥታ ዙሪያ በመምከር ለቀጣይ ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ጉባኤው በሚቀጥለው ሳምንት በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 22ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መወያያ አጅንዳ ይቀርፃል ተብሎ  ይጠበቃል።