ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መልሶ መቋቋም የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1/ 2007 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መንግስት መልሶ መቋቋም የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦማር አብዱላሂ አሊ ሻርማርኬን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በሶማሊያ የመልሶ መቋቋም ርብርብ ኢትዮጵያ ድጋፏን እንድምትቀጥል መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም “ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት፣ እንደ እህት አገር፤ ደግሞ እንደ ኢጋድ አባል አገርና እንደ ወቅቱ ሊቀመንበርነቷ ከዚህ ቀደም የምታደርገውን ድጋፍ የበለጠ አጠናክራ እንደምትቀጥል” አረጋግጠውላቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሻርማርኬ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ እስካሁን ላደረገችው ድጋፍ ኢጋድም ላሳየው ትብብር” ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገው ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍም የአገራቱ ግንኙነት ስትራቴጂካዊና በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በውይይታቸው የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም በሰፊው መክረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ በመንገድ ምህንድስና፣ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን፣ በአስተዳደርና በሌሎች መስኮች ለሶማሊያ ዜጎች ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በትምህርትና ስልጠና፣ በአቪዬሽን፣ በትራንስፖርት፣ በንግድና ሌሎች ስምንት መስኮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ የትብብር ስምምነት አላቸው።(ኢዜአ)