ሁለተኛው የኢትዮጵያና አሜሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ተካሄደ

አዲስ ኣበባ፤ መስከረም 27/2004 (ዋኢማ) – ሁለተኛው የኢትዮጵያና አሜሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን መካሔዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ሁለተኛው የኢትዮጵያና አሜሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም በዋሽንግተን ዲሲ ተካሒዷል፡፡

ፎረሙ የአሜሪካ ባለሃብቶችን በማነቃቃት በኢትዮጵያ መዋእለ ነዋያችውን እንዲያፈሱ ያለመ ሲሆን በበርካታ ድርጅቶች አማካኝነት እንደተዘጋጀም ለማወቀ ተችሏል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የአምስት አመቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠናከራ እየተገበረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ፎረሙ ሊያበረክተው የሚችለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አጋጣሚው ሀገሪቱ በጋራ ተጠቃሚኒት መርህ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ቱሪዝም ዘርፎች ትስስሩን ወደላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው አቶ ኃይለማርያም አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ልማትን በማፋጠን ድህነትን ለመቋቋም፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን እውን በማድረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ለማጠናከር ምቹ ፖሊሲዎች ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

መንግስት በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማቅረብ ለባለሃብቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የአሜሪካ ባለሃብቶች ኢንቨስት ለማድረግ መዳረሻቸው ኢትዮጵያ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ዶናልድ ያማሞቶ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በኢንቨስትመንትና ንግድ በተለይ በግሉ ዘርፍ ያላትን ትስስር ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም የአሜሪካ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ሰፊ የኢንቨሰትመንት አማራጭ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ምቹ ሁኔታና እያስመዘገበች ያለውን እድገት እድንቀዋል፡፡

በፎረሙ ላይ አቶ መኮንን ማንያዘዋልን ጨምሮ የሁለቱም አገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የግልና የማሕበራት ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ ባለሃብቶችና የኢትዮጵያ ዲያስፖራን ጨምሮ 400 ያህል ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።