ኢትዮጵያ ንፁህና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ሀይል ሀብቷን ለማሳደግ እቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገለፁ

አዲስ አበባ መስከረም 26/2004 (ዋኢማ) – ኢትዮጵያ ንፁህና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ሀይል ሀብቷን በማሳደግ የኢጋድ አባል አገራትን በሀይል አቅርቦት የማስተሳሰር እቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከኢትዮ-ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ምረቃ በኋላ ከጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ከተወያዩ በኋላ ገለፁ።

ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ፣ በአካባቢያዊና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነው የተወያዩ ሲሆን፤ ከውይይታቸው በኃላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጂቡቲ በነበራቸው ቆይታ ደስተኛ መሆናቸውን፣ በባቡርና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ከጂቡቲ ጋር ቀሪ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የሚቀጥሉ በመሆኑና የሁለቱ ሀገራት መጻኢ ግንኙነት ጠንካራና ብሩህ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት ኤሌክትሪክ ለማቅረብ በጀመረችው እንቅስቀሴ የመጀመሪያው በጂቡቲ መበሰሩም ያለምክንያት እንዳልሆነ ገልፀው፤ ከጁቡቲ ህዝብ ጋር ባለን የቀረበ ግንኙነትና ትስስር መነሻነት እንጂ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ንጹህ ታዳሽና ርካሽ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የበለጠ በማሳደግ በኢጋድ አገራት የተባበረና የተሳሰረ የኃይል አቅርቦት ማዕከል የመሆን እቅድ እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁት፡፡

የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌም በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስክ የጠነከረ ግንኙነት ያላቸው ኢትዮጵያና ጂቡቲ ለጋራ ብልጽግና አብረው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው ቆይታ በሶማሊያ ሰላምና ጸጥታ ላይም የተወያዩ ሲሆን፤ ጂቡቲ ወደ ሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ለመላክ መወሰኗንም ይፋ አድርጋለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ወንድም ለሆነው የሶማሊያ ህዝብ ሰላም መረጋገጥ ጂቡቲ ወታደሮች ለመላክ በመወሰኗ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም ከዚህ በፊት ወታደር ለላኩትም ሆነ ለጂቡቲ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ማረጋገጣቸውን ኢሬቴድን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።