የብድርና ቁጠባ ተቋማት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ ጥቅምት 20/2004/ዋኢማ/– የኢትዮጵያ አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ማኅበር ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ56 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታወቁ።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ወልዳይ አምሃ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ 28 አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማትና ሠራተኞቻቸው ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማበርከት በስፋት ተንቀሳቅሰው 56 ሚሊዮን 202ሺ 694 ብር መሰብሰብ ችለዋል።

በዚህም ረገድ 42 ሚሊዮን 980ሺ 647 ብር የሚሆነውን ተቋማቱ በቦንድ ግዢ ማበርከታቸውን የተናገሩት ዶክተር ወልዳይ፤ ቀሪው 13 ሚሊዮን 222ሺ 47 ብር በተቋማቱ ሥር የሚገኙ ከ10ሺ በላይ ሠራተኞች የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል።

ተቋማቱ ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅና ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረጉ የልማት ሥራዎች ሁሉ ግንባር ቀደም ሚና እንዳላቸው አመልክተው፤ በተለይም የግድቡ ዕውን መሆን በከፍተኛ ደረጃ የብድርና ቁጠባ ተጠቃሚ የሆኑት አነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት የኃይል አቅርቦት ችግርን ያቃልላል ብለዋል።

በመሆኑም ተቋማቱ ለህዳሴው ግድብ ግንባታም ሆነ በሀገሪቱ ላይ ለሚከናወኑ ማንኛውንም የልማት ሥራዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የአዲስ ብድርና ቁጠባ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋሽ አብተው በበኩላቸው፤ ለአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት በሀገሪቱ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ከልማቱ ጎን ለጎን የቦንድ ግዢው ዜጐች የመቆጠብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረው፤ በሀገሪቱም ፈጣን ልማት እንዲመጣ ያደርጋል ማለታቸውን የኢፕድ መግለፁን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።