ጃፓን በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ለኢትዮጵያ የ132 ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ፈረመች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 17/ 2004/ ዋኢማ/ – የጃፓን መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ለኢትዮጵያ የ132 ሚሊዮን ብር የምግብ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከፕሮግራሙ ጋር ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን የኢጣሊያ ርዕሰ መዲና በሆነችው በሮም ከተማ ውስጥ የተፈራረሙት በኢጣሊያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ማሻሩ ኮህኖና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሚር አብዱላ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ እንደገለጸው፤ የምግብ ድጋፉ የሚውለው በምሥራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በኢትዮጵያ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሕዝቦች ነው፡፡

የጃፓን መንግሥት በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ለኢትዮጵያ የምግብ ድጋፉን የሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ድጋፍ እንዲደረግ ባቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ መሰረት እንደሆነም ገልጿል፡፡

የጃፓን መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ አገራት ለተከሰተው የድርቅ አደጋ እስካሁን ለኢትዮጵያ፣ ለኬንያ፣ ለጂቡቲ፣ ለሱዳን፣ ለሶማሊያና ለደቡብ ሱዳን በዓለም የምግብ ፕሮግራም አማካኝነት ያደረገው ድጋፍ 524 ሚሊዮን ብር መድረሱን ኤምባሲው አስታውቋል፡፡

እንደ ኤምባሲው ገለጻ የጃፓን መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተ የድርቅ አደጋ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን፣ በዓለም የምግብ ፕሮግራምና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአፍሪካ ቀንድ ለሚያካሂዷቸው ተግባራት የ1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያና በኬንያ ለሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አስቸኳይ ድጋፍ የሚውል የ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

እንደ ኤምባሲው ገለጻ በአጠቃላይ የጃፓን መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ 127 ሚሊዮን ዶላር ወይም 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የኢዜአን ጠቅሶ ዋኢማ ዘግቧል።