ድርጅቱ በ1 ቢሊዮን ብር እያካሄዳቸው ያሉ አራት ከፍተኛ ፕሮጀክቶችን ግንባታ በቅርቡ እንደሚያጠናቅቅ አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2004/ዋኢማ/– በመንግስት በተመደበ 1 ቢሊየን ብር አራት ከፍተኛ የፕሮጀክቶች ግንባታ በቅርቡ እንደሚያጠናቅቅ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ የ11 ፕሮጀክቶችን ግንባታም በስምንት ቢሊዮን ብር እያካሄደ ነው፡፡

የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ቁምላቸው አበበ፤ እንደገለጹት ድርጅቱ ከሚያካሂዳቸው ኘሮጀክቶች መካከልም የሞጆ ደረቅ ወደብ፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአስተዳደር ሕንፃዎች፣ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የመስኖ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶችና የተንዳሆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚቀጥሉት አራት ወራት ይጠናቀቃሉ፡፡

የመስኖ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶቹ በቀጣዩቹ ሁለት አመታት ሲጠናቀቁ ከ150 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የማልማት አቅም እንደሚኖራቸውም አቶ ቁምላቸው ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ክልል የሚገኘው የተንዳሆ ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀከት መሆኑን ጠቁመው፤ ከ90 ሺ ሄክታር መሬት በላይ የማልማት አቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ከዚህም 60 ሺህ ሄክታሩ በአቅራቢያው ለሚገነባው የስኳር ፋብሪካ ግብዓት የሚሆን ሸንኮራ አገዳ የሚያመርት ሲሆን፤ ቀሪው ለአካባቢው አርብቶ አደሮች ለግጦሽና መስኖ ልማት የሚውል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የመስኖ ልማት የማስፋፊያ ፕሮጀክትም 7ሺህ 500 ሄክታር ተጨማሪ የመስኖ መሬት ለስኳር ፋብሪካው ዝግጁ የማድረግ ስራ 80 ከመቶ በላይ ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ ማደግን ተከትሎ የመጣውን በወደቦች ላይ የሚፈጠር መጨናነቅ ለመከላከል የሞጆ የደረቅ ወደብ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ወደቡ ከ5 ሺ በላይ እቃ የጫኑ ኮንቴይነሮችን በአንድ ጊዜ የማስተናገድ አቅም እንዳለው ጠቁመው፤ የግንባታ ስራው በሚቀጥሉት 3 ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጋር ተያይዞ በተንዳሆ የሚገነቡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 15 የአስተዳደር ሕንፃዎች ግንባታ በአሁኑ ወቅት 80 በመቶው መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ለፕሮጀክቱ ባለቤት እንደሚያስረክብም አመልክተው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ለሚመሠረቱ መንደሮች የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማቅረብ የሚካሄደው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስራ እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ግንባታውም በቀጣዩቹ ሦስት ወራት እንደሚጠናቀቅ ገልፀው፤ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁት ፕሮጀክቶች መንግስት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችን ለማሳካት የአገሪቱን ህዳሴ እውን ለማድረግ ካለማቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸው ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ ደረጃ የሚካሄዱ የ11 ፕሮጀክቶችን ግንባታም በስምንት ቢሊዮን ብር እያካሄደ መሀኑን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችል ሕንፃ ግንባታ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያስገነባ መሆኑንም ኢዜአን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግባል።