በደቡብ የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገዶች የሚያገናኝ የ14 ሺ ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ተጀመረ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 16/2004/ዋኢማ/– በደቡብ ክልል የገጠር ቀበሌዎችን ከዋና መንገዶች የሚያገናኝ 14ሺ ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ መጀመሩን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አስታወቀ ::

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ በክልሉ በሚገኙ 14 ዞኖችና 136 ወረዳዎች ውስጥ ነው ::

የመንገዶቹ መገንባት በክልሉ ሕዝቦች መካከል ከሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ትስስር በተጨማሪ በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሠፊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ የኔወርቅ ቁምላቸው ገልፀዋል::

የመንገድ ግንባታውን ወደ ተግባር ለማሸጋገር ለየዞንና ለወረዳ የንግድና  ኢንዱስትሪ መምሪያ አመራሮችና የከተማ ከንቲባዎች በፕሮግራሙ ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን  ባለሙያው አስረድተዋል ::

የመንገድ ስራው የሚከናወነው በግንባታ ዘርፍ ለመሠማራት በተደራጁ ማህበራት አማካኝነት መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው ቢሮው በሥራው የሚሳተፉ ማህበራትን በስልጠና በገንዘብና በቁሳቁስ በማጠናከር የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል::

በመንገድ ግንባታው የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት እንዲሳተፉ የተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በፕሮግራሙ መሳተፋቸው መንገዱ ለክልሉ ልማት ከሚያበረክቱት አስተዋፆ በተጨማሪ በቀጣይ የሙያ ክህሎታቸውንና የካፒታል አቅማቸውን በማጎልበት ወደ መካከለኛና ከፍተኛ የሥራ ተቋራጭነት ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል::

የሚገነቡት መንገዶች 3ሺህ 680 ቀበሌዎችን ክረምት ከበጋ ከዋናው መንገዶች ጋር የሚያገናኙ ሲሆኑ፤ ይህም የክልሉን የመንገድ ኔትዎርክ በማስፋት የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል መጠቆማቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።