የአራት አገራት ኤምባሲዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2004/ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ የሚገኙ የአራት አገራት ኤምባሲዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህብረተሰቡን ለሚጠቅሙ የልማት ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ።

ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ያረጋገጡት ኢምባሲዎች የእንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ እና የኔዘርላንድ ኤምባሲዎች ናቸው።

ኤምባሲዎቹ በአሶሳ ከተማ በተካሄደው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ ለማሳየት በተዘጋጀው ኤግዚቪሽን ላይ ከተሳተፉ በኋላ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ገልጸዋል።

ኤምባሲዎቹ በክልሉ ከሚገኙ ከቤኒሻንጉል መልሶ ማቋቋም፣ ከትኩረት ለጉሙዝ፣ ከቦሮ ሽናሻ፣ ከአሶሳ አካባቢ ጥበቃ ልማት ማህበር እና ከትምህርት ለልማት ማህበራት ጋር በቅንጅት ለመስራት መወሰናቸውን ኢዜአን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘግቧል።