ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወደ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2004/ዋኢማ/–  ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚገኘውን አመታዊ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በአምስት አመቱ እቅድ ማብቂያ ላይ ወደ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማድረስ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደገለጹት በዕድገትና ትራንስፎርሚሸን ዕቅዱ መሰረት የኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚናውን ሊረከብ በሚያስችለው መሰረት ላይ ይገኛል፡፡

ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በ2003 ዓ/ም የተገኘው ገቢ 208 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚጠጋ እንደነበር ጠቁመው፤ ይህም ከ2002 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ89 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ እየታየ የመጣውን ዕድገት በማስቀጠልም በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ 2 ነጥብ 63 ቢሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በእድገትና ትራንፎርማሽን እቅድ ዘመኑ የተቀመጠው ግብ በ2001 አመተ ምህረት ከነበረው ጠቅላላ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ23 እጥፍ ብልጫ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪው መስፋፋትም ለአጠቃላዩ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድልን በመፈጠርና በማህበራዊ መስኮች ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የተቀመጡ ዓላማዎችና ግቦች በተቀመጡላቸው አማራጭ ስትራቲጂዎች ላይ ተመስርተው እንዲተገበሩ በተለይ ለመካከለኛና ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ልዩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ድጋፍና ክትትል ከሚደረግላቸው ውስጥም የጨርቃ ጨርቅ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችና አግሮ ፕሮሰሲንግ እንደሚገኙበት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ እነዚህም በርካታ የሰው ኃይልና የግብርና ምርቶችን በስፋት የሚጠቀሙና ኤክስፖርት መር መሆናቸውን የኢዜአ ዘገባ እንደሚያመለክት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጠቁሟል።