ባንኩ 61 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 20/2004/ዋኢማ/ – የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር በ2003 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት ከ61 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ገብረመድህን በሸራተን አዲስ የባንኩ 7ኛ መደበኛ ጉባኤና 3ኛ ድንገተኛ ስብሰባ ላይ እንደገለፁት፤  የተገኘው 61 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በበጀት ዓመቱ እቅድ ክንውን አፈፃፀም ባንኩ አከናውናቸዋለሁ ብሎ ያቀዳቸውን ዋና ዋና ተግባራት በተፈለገው መንገድ ማሳካት በመቻሉ ነው።

ባንኩ ያገኘው ትርፍ ከባለፈው የበጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ24 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልፀው፤ ካገኘው ትርፍ ላይም ለባለአክሲዮኖች ለሁለተኛ ጊዜ የ11 በመቶ የትርፍ ክፍፍል እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ከተገኘው አጠቃላይ ትርፍም 18 ነጥብ 1 ሚሊየን ብር ለመንግስት ግብር የተከፈለ መሆኑን ዶክተር ብርሃኑ ጠቁመው፤ ቀሪው ለባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል፣ ለተቀማጭና ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ እንደሚውልም ገልፀዋል።

የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን እዳውም ወደ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን መድረሱን ዶክተር ብርሃኑ ገልፀው፤ በበጀት ዓመቱ ከ676 ሚሊየን ብር በላይ ለተበዳሪ ደንበኞች ብድር መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።

የመመለሻ ጊዜያቸው የደረሱ ብድሮችን ተከታትሎ በመሰብሰብ ረገድም ከቀዳሚው ዓመት በ92 በመቶ ብልጫ ያለው ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ባንኩ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለሀገር ውስጥ ንግድና አገልግሎቶች ሥራ ማስኬጃ እንዲሁም ለወጪና ገቢ የንግድ ዘርፍ የተሰጠው ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፤ ለኮንስትራክሽንና ህንፃ ግንባታ፣ ለግብርናና ሌሎች ዘርፎችም ብድር መስጠቱን ተናግረዋል።

የሚሰጠውን አገልግሎትና ተደራሽነቱን በማስፋት በኩልም ባንኩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፈው የበጀት ዓመትም በጥናት በተረጋገጠባቸው የሀገሪቱ ከተሞች አምስት ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የባንኩን ቅርንጫፍ ቁጥር ወደ 29 ማድረስ ችሏል።

በአሁኑ ወቅትም የባንኩ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም 59ሺ 300 መድረስ የተቻለ ሲሆን፤ የባንኩን የቁጠባና የተቀማጭ ገንዘብና የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ባንኩ በ2004 የበጀት ዓመትም ከታክስ በፊት ከ112 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ለማግኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፤ እቅዱን ለማሳካትም ማኔጅመንቱና ሰራተኛው እንዲሁም ባለ አክሲዮኖች በጋራ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ባንኩ ለታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬትም 164 ሚሊየን ብር ቦንድ በመግዛት ለሀገር አለኝታነቱን ማሳየት የቻለ መሆኑንም ዶክተር ብርሃኑ ተናግረዋል።

በጉባኤው ላይም አዳዲስ የአክሲዮኖች ዝውውርን የፀደቀ ሲሆን፤ የባንኩ የ2002/2003 አጠቃላይ ሪፖርትና የ2003/2004 እቅድ ለጉባዔተኛው ቀርቦ ውይይት ከተካሄደባቸው በኋላ ፀድቋል።

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ አራት ዓመታትን ያስቆጠራ ሲሆን፤ 7ሺ ባለአክሲዮኖችን በመያዝ እየሰራ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።