ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በአካባቢው ሰላምና ጸጥታን የበለጠ ለማስፈን በጋራ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 21/2004/ዋኢማ/ – ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በአካባቢው ሰላምና ጸጥታን የበለጠ ለማስፈን በጋራ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አህመድ መሐመድ በሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ያላቸውን የትብብር ግንኙነት ስለ ማሳደግ፣ እንዲሁም በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።

በህንድ ውቅያኖስና በሶማሊያ የባህር ዳርቻ የሚፈጸመውን የባህር ላይ ዘረፋንና የውንብድና ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠርም የበለጠ ተቀራርበው መስራት የሚቻልባቸውን ብልሃቶች አንስተው መክረዋል።
ፕሬዝዳንት አህመድ መሐመድ አገራቸው የባህር ላይ ወንበዴዎችን በመከላለክና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፤ በውንብድና ተግባር ላይ ተሳትፎ የነበራቸው በርካታ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በመታዬት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ሶማሌላንድ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም የሚባል ወዳጅነት እንዳላት የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ግንኙነቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ለማድረግ በሁለቱም ወገኖች በኩል እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በበኩላቸው በሶማሊያ የባህር ዳርቻ የሚንቀሳቀሱ የባህር ላይ ወንበዴዎችን ድርጊት ለማስቆም ሶማሌላንድ እያደረገች ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በድንበሮቻቸውና በአካባቢው ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን በጋራ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ መለስ ለፕሬዚደንት አህመድ ማረጋገጣቸውን ውይይቱን የተከታተሉ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ኢዜአን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።