በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የስኳር ህመም በመከላከል በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ

አዲስ አበባ ጥቅምት 21/2004/ዋኢማ/ – በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የስኳር ህመምና ተያያዥ የሆኑ የጤና ችግሮች በመከላከል በኩል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ።

ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በሸራተን አዲስ የአውሮፓ የስኳር 6ኛው አለም አቀፍ ስልጠና ላይ እንደተናገሩት፤ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውን የስኳር ህመም ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል።

ሀገሪቱ ቀደም ባሉት አመታት ኤችአይቪ/ኤድስን፣ የሳንባ ነቀርሳ በሽታንና የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ያደረገችውን ጠንካራ እንቅስቃሴ በስኳር ህመም ላይም መድገም ይገባታል ብለዋል።

ስልጠናው በኢትዮጵያ መካሄዱ ወቅታዊ መሆኑን የገለፁት አቶ ኃይለማርያም የህክምና ባለሙያዎቹ ስልጠናውን እንዲያገኙ መደረጉ ትልቅ አጋጣሚ ከመሆኑም ባሻገር የጤና ባለሙያዎቹ ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው 366 ሚሊየን የሚገመቱ ወገኖች የስኳር ህመምተኛ መሆናቸውን መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ተናግረዋል።

እስከ አሁንም 4 ነጥብ 6 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በስኳር ህመም ህይወታቸውን ማታጣቸውን ገልፀው፤ ለህሙማኑ የህክምናና እንክብካቤም ከግማሽ ትሪሊየን ዶላር በላይ በአመት ወጪ እንደወጣም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር ፕሬዚዳንትና የስልጠናው አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር ዶክተር አህመድ ረጃ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የስኳር ህመም የዓለምን ህዝብ ከሚያሳስበው ችግሮች አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በወረርሽኝ መልክ እየተስፋፋ ያለውን የስኳር ህመም ለመግታት የጤና ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግና የእውቀት ክህሎታቸውን ማስፋት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 366 ሚሊየን የሚገመት የህብረተሰብ ክፍል ከስኳር ህመም ጋር መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር አህመድ መላው ህብረተሰብ ህመሙን እንዲከላከል ማድረግ ካልተቻለ አሁን ያለው ቁጥር ወደ ግማሽ ቢሊየን ሊያድግ እንደሚችል ገልፀዋል።

ለጤና ባለሙያዎቹ የሚሰጠው ስልጠና እውቀታቸውን ለማዳበርና የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት እንዲያሻሽሉ የሚረዳ ሲሆን፤ ስልጠናው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሀገሪቱን በጎ ገፅታ ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚከፍትም ዶክተር አህመድ ተናግረዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከ20 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የጤና ባለሙያዎችና ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተውጣጡ 160 የጤና ባለሙያዎች በስልጠናው የሚሳተፉ ሲሆን፤ ስልጠናውንም ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኡጋንዳና ታንዛኒያ የተውጣጡ ታዋቂ ሀኪሞችና ሳይንቲስቶች  እንደሚሳተፉበት ተገልጿል።

ስልጠናውን የአውሮፓና የአሜሪካ ስኳር ህመም ማህበሮች፣ አለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን የአፍሪካ ሪጅን ጽህፈት ቤትና የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር በጋራ በመሆን ማዘጋጀታቸውን ዶክተር አህመድ መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።