በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ያለው የባሕል ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2004/ዋኢማ/ – በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ያለው የባሕል ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሒሮዩኪ ኪሽኖ እንደገለጹት የሁለቱ አገራት የባሕል ግንኙነት በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለፃ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 2011 የኢትዮ-ጃፓን ተማሪዎች ማሕበር በሁለቱ አገራት ህዝቦችና መንግስታት መከካል ያለውን የወዳጅነትና የባህል ትስስርን ማጠናከር ዓላማ ያደረገ ስብሰባ ማካሔዱን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የአድዋን የድል በዓል በመጋቢት ወር ሲያከብሩ የጃፓን የጃዝ ቡድን አዲስ አበባ ውስጥ ዝግጅቱን ያቀረበ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ወቅትም አመታዊው የጃፓን የልጃገረዶች ፌስቲቫል በኢትዮጰያ የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት በደመቀ ሁኔታ መከበሩን አስረድተዋል፡፡

በእለቱም ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ፒያኒስት ግርማ ይፍራሸዋ ዝግጅቱን አቅርቧል፡፡ የሁለቱን አገራት የባህል ግንኙነት ከማጠናከር አኳያም እ.ኤአ. በመስከረም 2011 ለሶስት ሳምንታት የቆየ የጃፓን የሸክላ የጥበብ ሥራዎችን የሚያሳይ ኤግዚቪሽን በጎተ ገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የአርት ሙዚየም መካሔዱንም አብራርተዋል፡፡

ኤግዚቪሽኑ የተዘጋጀበት ዋና አላማ የጃፓንን ባሕል ማስተዋወቅና የሁለቱ አገራትን የግንኙነት መሰረት ለማጠናከር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ትናንት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ አለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል ላይ የጃፓንም ፊልሞች ቀርበው እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከፊልሞቹ ውስጥ አንደኛው ጃፓን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1950ዎቹ ምን እንደምትመስልና ታከናውን የነበረውን የልማት ሁኔታ ያሳያል፡፡ ይህም ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የእድገት ጎዳናእንደ ማነጻጸሪያ ለማሳየትያስችላል ብለዋል፡፡

በአለፈው አመትም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ለሚገኘው ታሪካዊ ጥናት እንዲያግዝ ለብሔራዊ ሙዚየም 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ እርዳታ መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

ባሕል ሕዝቦችን ለማስተሳሰር ዋነኛ መሳሪያ ሲሆን በኢትዮጵያ የቡና በጃፓን ደግሞ የሻይ ስነ-ስርዓቶች የአገራቱን ባሕል ለማስተዋወቅ እንደ ድልድይ ያገለግላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።