የተንዛዛ የባለ ጉዳዮች ምልልስ ማስቀረት የሚያስችሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 7/2004/ ዋኢማ/– የተንዛዛ የባለ ጉዳዮችን ምልልስ ማስቀረት የሚያስችሉ የአገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገለፁ።

የኢፌድሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ባለፉት አመታት ስር ሰደው ከቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ ዜጎች ተደራሽና ቀልጣፋ ፍትህ ሳያገኙ ቆይተዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ዋና ዋና ችግሮች በጥናት ተለይተው ማሻሻያ እንዲደረግባቸው በተወሰደው የመፍትሄ እርምጃ ያለቀለት ባይሆንም አበረታች ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ዳኞች በአመለካከትና በአቅም ረገድ የሚታዩባቸውን ችግሮች በስልጠናና በተዛማጅ ድጋፎች እንዲቀርፍ የተሰሩት ተከታታይ ሥራዎች ለተመዘገበው ውጤት የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ከፕሬዚዳንቱ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

ከዚህ ቀደም የአንድ መዝገብ አማካይ እድሜ ከ7 እስከ 8 ዓመት እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ተገኔ አሁን በተካሄደው መሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ትግበራ በሳምንታት እንዲያጥር ተደርጓል።

በዳኞች ይሁንታና በተለምዶ በሚደረገው የህግ ትርጉም በጥፋተኞች ላይ ይጣል የነበረው ቅጣት በአወሳሰን መመሪያ እንዲፈፀም መደረጉ፣ ዜጎች በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያላቸውን ግልፀኝነትና አመኔታቸው እንዲጨምር የረዳቸው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

አቶ ተገኔ እንደሚሉት ዳኞች በተገልጋዮች ላይ ቅሬታ ሊፈጥሩ በሚችሉ ድርጊት ተሰማርተው መገኘታቸው በተጨባጭ መረጃ ሲደገፍ ተገቢ የሆነ እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።